ቱርክ በኢትዮጵያ የፎረንሲክ ምርምራ ተቋምና ስርዓት ማሻሻያ ስራዎች ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች

89

ነሐሴ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) ቱርክ በኢትዮጵያ የፎረንሲክ ምርምራ ተቋምና ስርዓት ለማሻሻል እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች።

የፍትሕ ተቋማት ሰራተኞችና አመራሮች በቱርክ የትምህርትና ስልጠና እድል የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው ብላለች።

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አንተአለም አግደው በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ ጋር በፍትሕ ዘርፉ እየተካሄዱ በሚገኙ የለውጥ ስራዎች እና ዘርፉን ለማጠናከር ሊደረጉ በሚገባቸው የሁለትዮሽ የፍትሕ ትብብሮች ዙሪያ ዛሬ ውይይት አካሂደዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በውይይቱ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያና በቱርክ መንግስት ኃላፊዎች መካከል በፍትሕ ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከር የተካሄዱ ውይይቶች ወደ ትግበራ መግባት እንዳለባቸው ተነስቷል።

የኢትዮጵያን የፎረንሲክ ምርመራ ተቋምና ሥርዓት ለማሻሻል እና ለማዘመን የቱርክ ፎረንሲክ ኢንስቲትዩት ድጋፍ የሚያደርግባቸው መስኮች መለየታቸውን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

በዚህ ረገድም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና አመራሮች የአጭርና የረጅም ጊዜ ትምህርትና ስልጠና የአቅም ግንባታ ሥራዎች በትብብር እንደሚሰራ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል ነው የተባለው።

የቱርክ ሀገር የትምህርትና ስልጠና ተቋማት የዐቃቤ ሕግ፣ የፖሊስ እና የፍርድ ቤት ተቋማት አመራርና ሰራተኞች የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድሎችን ጨምሮ ሌሎች ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ተመልክቷል፡፡

በተጠቀሱት ጉዳዮች ዙሪያ የመግባቢያ ሰነዶች በሁለቱ አገራት የሚመለከታቸው አቻ ተቋማት አመራሮች መካከል በቅርቡ እንዲፈረሙ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን የሥራ ኃላፊዎቹ ባደረጉት ውይይት ወቅት ተገልጿል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም