ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን መጠቀም የንግድ ስርዓቷን ለማቀላጠፍ ያስችላታል - ንግድ ሚኒስቴር

83
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ወደብ በተጨማሪ የአሰብ ወደብን መጠቀሟ የንግድ ስርዓቷን ይበልጥ የተቀላጠፈ ለማድረግ እንደሚያስችላት የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ኢትዮጵያ በንግዱ ዘርፍ ተወዳዳሪነቷን ለማስፋት አማራጭ ወደቦችን መጠቀም ያስፈልጋታል። ለዚህም በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት መካከል የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የተደረሰው ስምምነት ለህዝቦች ታላቅ እድል ነው፡፡ ''የአሰብ ወደብ አላስፈላጊ የሆኑ የሎጂስቲክስ እና የትራንስፖርት ወጪዎችን ለመቀነስ አሰተዋፆኦ ያበረክታል'' ሲል መግለጫው አትቷል። ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያና የኤርትራን ዘላቂ ግንኙነት እንዲያግዝ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚኖረውን የንግድ ግንኙነት መልክ ለማስያዝ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁሟል። የአሰብ ወደብን በመጠቀም የንግድ ስርዓቱን ማሻሻል በሚቻልበትና ምን ምን አገልግሎቶችን በቅርቡ መጀመር እንዳለባቸው ለመለየት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ  በመግለጫው ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም