የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በ25 አዳዲስ የትምህርት አይነቶች ስልጠና ለመጀመር ዝግጅት አድርጓል

114

ጋምቤላ ነሀሴ 11/2014 (ኢዜአ ) ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ የትኩረት አቅጣጫ በሆኑ የልማት ዘርፎች የሚፈለገውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት በሚያስችሉ 25 አዳዲስ የትምህርት አይነቶች ስልጠና ለመጀመር ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በተያዘው 2015 የትምህርት ዘመን በሚከፍታቸው አዳዲስ የትምህርት አይነቶች ስልጠና ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማከናወኑን አመልክቷል።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ከተማ ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በ2015 የትምህርት ዘመን ስልጠና የሚሰጥባቸው አዳዲስ የትምህርት አይነቶች በማዕድን፣ በቱሪዝም እንዲሁም በግብርና ተፈጥሮ ሀብቶች ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ከትምህርት መስኮቹ መካከል 10ሩ በሁለተኛና 15ቱ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የሚሰጡ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

ዩኒቨርሲቲው በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሀ ግብር ስልጠና ከሚጀምርባቸው የትምህርት አይነቶች መካከል የፔትሮሌም ምህንድስና፣ የማህበረሰብ ጤና፣ የአንትሮፖሎጂ፣ የሆቴልና ቱሪዝምና  የሒሳብ የትምህርት አይነቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።

ዩኒቨርሲቲው በ2015 የትምህርት ዘመን ተማሪዎቹን በተሟላ የስልጠናና የማህበራዊ አገልግሎት ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ ከሚገኙት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መካከል መሰረተ ልማት፣  የተማሪዎች አገልግሎት፣ የመምህራንና ሌሎች የሰው ኃይልን የማሟላት ተግባራት  እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ጌታሁን ታደሰ በበኩላቸው በ2015 የትምህርት ዘመን ለተማሪዎች የጽንሰ ሃሳብና ተግባር ተኮር ትምህርቶችን አጣጥሞ ለመስጠት ቤተ ሙከራዎችን የማደረጃት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ካሁን በፊት ዩኒቨርሲቲው በበቂ ሁኔታ ቤተ ሙከራ ባለመደራጀቱ ተማሪዎችን ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች  በመላክ ተግባር ተኮር ስልጠናዎችን ይወሰዱ እንደበር አስታውሰው  "አሁን ላይ ችግሩን ለማስቀረት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በአዲሱ የትምህርት ዘመን ለተማሪዎች ጥራቱን የጠበቀ ስልጠና በመስጠት የግብዓትና የመምህራን አቅም የማጠናከር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ድግሞ የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ዳሬክቶሬት ዳሬክታር ዶክተር ኒያል ቷች ናቸው።

ካሁን በፊት ተማሪዎች የሶስትና አራት ዓመት ስልጠናቸውን አጠናቀው ቢወጡም በስራ ላይ ውጤታማ የማይሆኑበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው ችግርሩን ለማስቀረት ዩኒቨርሲተው የመውጫ ፈተና ለመስጣት እየተዘጋጀ መሆኑን አመላክተዋል።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው 2015 የትምህርት ዘመን አዲስ በሚጀምራቸው የትምህርት ዘርፎች የቅድመ ምረቃ ስልጠና ዘርፎቹ ወደ 46 እንዲሁም  የድህረ ምረቃ ስልጠና ዘርፎቹ ወደ 13 ከፍ እንደሚሉ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም