የአስተዳደር ወሰን የማካለል ስራው የህዝቦችን ተጠቃሚነትና ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥ ነው

170

ነሐሴ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የአስተዳደር ወሰን የማካለል ስራ የህዝቦችን ተጠቃሚኒትና ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ገለፁ።

በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የአስተዳደር ወሰን የማካለል ስራ የሁለቱ አካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚኒት የሚያረጋግጥ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ገለፁ።

በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ህዘብ የጋራ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን የማካለሉ ስራ የህዝቦችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱም ነው የተጠቆመው፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የአስተዳደር ወሰን የማካለል ስራው የህዝቦችን አንድነትና አብሮ ማደግ የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የአስተዳደር ወሰን ባለመኖሩ ምክንያት በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ሲያስነሳ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ይህም ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።
የአስተዳደር ወሰን የማካለል ስራ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ከመሆኑም በላይ የህዝቦችን ሰላምና አንድነትና ትስስር የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የመንግስት የልማት ተቋማት አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ፣በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የወሰን ማካለል ስራው መከናወኑ በሁለቱም ወገን የልማት ስራዎች በተቀላጠፈ መልኩ እዲከናወን የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው አስተዳደራዊ ወሰንን የማካለሉ ጉዳይ ለረዥም ጊዜ ሲንከባለል የመጣ የህዝብ ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።

ጉዳዩ በህግ አግባብ እልባት ማግኘቱም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ብሎም ልማትን ለማፋጠን የመፍትሄ አቅጣጫ ሆኖ መቀመጡን አንስተዋል።

በኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የከተማ ፖለቲካ አደረጃጀት ሃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ፤የአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳደራዊ ወሰን የማካለሉ ስራ የሁለቱነም ወገን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ዘላቂ ሰላም፣የጋራ ልማትና የህዝቦችን በትብብር የመኖር እሴት የሚያጎለብት እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሞላ ንጉስ የአስተዳደር ወሰን ስራው የኢፌዴሪ ህገ መንግስትን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተርን እና የኦሮሚያ ክልል ህገ-መንግስትን መሰረት አድርጎ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወሰን ማካለል ስራው የአስተዳደራዊ ስራዎችንና የጋራ ልማትን በተሳለጠ መልኩ ለማስኬድ የሚያግዝና የሁለቱም አካባቢ ነዋሪዎች የጋራ እሴት ይበልጥ የሚያጠናክር እንደሆነም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም