በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን የማካለሉ ስራ የህዝቦችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደረሰ

198

ነሐሴ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን የማካለሉ ስራ የህዝቦችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን የሁለቱ አስተዳደር አመራሮችና የህዝብ ተወካዮች ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ማካለል ላይ በሁለቱ ወገኖች የተደረሰ ስምምነት ላይ ህዝባዊ ውይይት ተካሄዷል።

በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ አገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ የተደረሰው ስምምነት የህዝቦችን አንድነትና አብሮ ማደግ በሚያጠናክርና መልኩ  እንዲተገበር ማድረግ  ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የአስተዳደር ወሰን ባለመኖሩ ምክንያት በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ሲነሳ  መቆየቱም ነው በመድረኩ የተገለጸው፡፡

በተለይ መሰረተ ልማት ዝርጋታና ወሳኝ የሆኑ የልማት ስራዎችን ለመስራት እንዲሁም የመሬት ወረራን ጨምሮ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮ መቆየቱን ነው የመድረኩ ተሳታፊዎች ያነሱት፡፡

ከተማ አስተዳደሩና ልዩ ዞኑ ተቀናጅተውና ተደጋግፈው በጋራ እንዳያድጉና እንዳይለሙ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱም እንዲሁ፡፡

በመሆኑም የአስተዳደር ወሰን ጉዳይን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ከከተማ አስተዳደሩና ከልዩ ዞኑ የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥልቅ ጥናት ማካሄዱም ተገልጿል፡፡

የአስተዳዳር ወስን መካለል የህዝቦችን ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክር፣ ዘላቂ የህዝቦችን ኢኮኖሚያዊ እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

ይህ የወሰን ማካለል ሂደት ተግባራዊ ሲደረግም የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት፣ የኦሮሚያ ክልል ህገ-መንግስትና የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር እንደመነሻ ተወስዷል ነው የተበባለው ፡፡

የአስተዳዳር ወሰኑ በህዝቦች ስምምነት መሰረት ማካለል ደግሞ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡  

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአስተዳደር ወሰን ለዘመናት ምላሽ ሳይሰጠው መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በመሆኑም የአስተዳደርና ወሰን ጥያቄ የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት ለማጎልበት በማሰብ ተግባራዊ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡  

ውሳኔው ከወሰን ባሻገር የህዝቦችን አብሮ መኖር እሴት የሚያጠናክር፣ አብሮነትን የሚያጎለብትና ሁለቱንም ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ይህ ውሳኔ ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜ በሁለቱም አካባቢ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት እንደቀደመው ሁሉ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ መልኩም የአካባቢዎቹን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተግባር በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም ባሉበት የሚቀጥሉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡    

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም ውሳኔው የህዝቦች አብሮ የመኖር እሴት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቴክኒክ ኮሚቴው እስካሁን ያከናወነው ተግባር የሚደነቅ መሆኑንም እንዲሁ፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም