በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል-የጤና ሚኒስቴር

238

ነሐሴ10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የበሽታዎቹን ስርጭት ለመግታትና ለማከም በሚቻልበት ሂደት ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደገለፁት ስኳር፤የልብና የደም ቧንቧ ችግር፤ግፊት፤ካንሰር፤ኩላሊትና የአእምሮ ጤና ችግር በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለማከም የአንድ ሴክተር ስራ ብቻ ሊሆን አይችልም ያሉት ዶክተር ደረጀ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በተለይ በከተሞች አካባቢ እየተረሳ የመጣውን የእግር ጉዞና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለማድረግ፤አልኮል፤ሲጋራ ማጨስ፤ስኳርና የቅባት ምግቦች በስፋት መመገብ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት እንዲስፋፋ ዋና ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከምና ለመከላከል የሚያስችል አዲስ ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በተለይም ህብረተሰብ አቀፍ ንቅናቄ መፍጠርና የህዝቡ የአመጋገብ ዘይቤ እንዲለወጥ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የዕለት ተዕለት ተግባር እንዲሆንና እንዲዳብር ለማስቻል ጭምር በጋራ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በዚህም የበሽታዎችን ስርጭት በ50 በመቶ መቀነስ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

በመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ላይ መንግስት በሙሉ አቅም እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ የህዝብ መድሀኒት ቤቶችን የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የጨረር ህክምናን በክልሎች ሆስፒታሎች የማስፋፋት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም በጂማ፤ሐሮማያ፤ጎንደር፤ሀዋሳና ሌሎች አካባቢዎች ህክምናውን ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም