የ"ብሉ ኢኮኖሚ" ዘርፉን ይበልጥ በማልማት ድርቅን መቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ አማራጭ መጠቀም ይቻላል-ኢጋድ

105

ነሃሴ 10/2014/ኢዜአ/ የ"ብሉ ኢኮኖሚ" ዘርፉን ይበልጥ በማልማት ድርቅን መቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ አማራጭ መጠቀም ይቻላል ሲል የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) ገለፀ።

በዓሳ ሀብት ላይ ያተኮረው  ሁለተኛው የኢጋድ ‘ብሉ ኢኮኖሚ' የልምድ ልውውጥ አውደ-ጥናት በኢዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ አውደ-ጥናት ላይ ሁሉም የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

"ብሉ ኢኮኖሚ" የውቅያኖስ፣ የሐይቅና የባህር ሀብቶችን እንዲሁም ወደቦችን ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋልን ማዕከል ያደረገ ነው።

የኢጋድ  የአካባቢ ጥበቃና ዘላቂ ልማት ፕሮግራም ኃላፊ ዶክተር እሸቴ ደጀኔ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አውደ- ጥናቱ የኢጋድ አባል ሀገራት በ'ብሉ ኢኮኖሚ' ያላቸውን ተሞክሮ ማጋራት የሚያስችል ነው ብለዋል።

አባል ሀገራቱ በ'ብሉ ኢኮኖሚ' ትልቅ የመልማት አቅም ቢኖራቸውም ይህን አቅም እምብዛም እየተጠቀሙበት አይደለም ብለዋል።

ከዚህ ዘርፍ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን በትራንስፖርት፣ በቱሪዝም፣ በዓሳ ሀብት ልማትና በሌሎች አካታችና ዘላቂ የውቅያኖስ፣ የሐይቅና የባህር ሀብቶች አጠቃቀም መፍጠር ያለመ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉን በዘላቂነትና በትብብር መጠቀም የሚያስችል መዋቅር ለመዘርጋት ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

በዚሁ መሰረት የኢጋድ አባል አገራት ዓሳን በስፋት በማርባት ድርቅን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ አማራጭ መጠቀም የሚያስችል አቅም መኖሩን ተናግረዋል።

ይህንኑ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የመገናኛ ብዙኃንም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባለ ብዙ ወንዞችና ሐይቆች ባለቤት በመሆኗ  በ‘ብሉ ኢኮኖሚ’ ዘርፍ ሰፊ የመልማት አቅም አላት ብለዋል።

በዚህም የአሥር ዓመት እቅድ ተዘጋጅቶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልፀው፤ በአጠቃላይ ካለው አቅም አንጻር ሥራው ጅምር ላይ መሆኑን ነው የገለጹት።

ሀገሪቱ ያሏትን ወንዞች በማልማት ከዚህ የሚገኘውን ጥቅም በአግባቡ ለመጠቀም እየሰራች መሆኑና ሥራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳይ አማካሪ አነኔ ቀጄላ ኢትዮጵያ በቂ የውሃ ሀብት ያላት በመሆኑ ከዚህ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ማግኘት ትችላለች ብለዋል።

ዘርፉ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር በስፋት ከተሰራበት የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ድርቅን ለመቋቋም አጋዥ መሆኑንም አክለዋል።

በተጨማሪም በወደቦች ልማት ዘርፉ በ'ብሉ ኢኮኖሚ' አማካኝነት በርካታ ጥቅሞች ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል።

ከውሃ ጋር የተሳሰረ ኢኮኖሚ ወይም ውሃ ወለድ ኢኮኖሚን ተግባራዊ የሚያደርገው "ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ" ለአምስት ዓመታት እንደሚተገበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም