በተያዘው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

231

ነሐሴ 10 ቀን 2014(ኢዜአ) በተያዘው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የ2014 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ አፈፃፀምና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 12 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ገልጸዋል።

አፈፃፀሙም አገሪቷ ከነበረችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ጥሩ የሚባል መሆኑን ጠቅሰው በተያዘው በጀት ዓመትም የተጠናከረ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።\

May be an image of 10 people, people sitting and indoor

በግብርናው ዘርፍ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በአይነትና በመጠን በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የወጪ ንግድ አፈፃፀሙ ዕድገት እያሳየ ቢሆንም በቅባት እህሎች የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ግን ብዙ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

በ2014 በጀት ዓመት የጥራጥሬና ቅባት እህሎች የወጪ ንግድ አፈፃፀም ሰሊጥና ኑግ የተሻሉ ሲሆን በጥራጥሬ እህሎች ረገድ ደግሞ ማሾ፣ ቦለቄና ሌሎችም ጥሩ አፈፃፀም የታየባቸው መሆኑ ተገለጿል።

በ2014 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ አፈፃፀም ከ2013 በጀት ዓመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር በ14 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማሳካት ካለፈው በጀት አመት በ29 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል ።

በ2015 በጀት ዓመት ከቅባትና ጥራጥሬ እህሎች ወጪ ንግድ 595 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ እንደታቀደም ነው የተናገሩት።

የጥራጥሬ እህሎች 262 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ድርሻ ሲኖራቸው የቅባት እህሎች ደግሞ 333 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ታቅዷል።

ለዕቅዱ ስኬት የአገር ውስጥ የምርት ክምችትን መቀነስ፣ በላኪዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥርን ማጠናከርና ተገቢው ድጋፍ መስጠት፣ ሕገወጥነትን መከላከል፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የአሰራር ስርዓትን የማዘመን ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተጨማሪም ዘርፉን በቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የምርት መዳረሻ አገራትን ማስፋት፣ የወጪ ምርቶች መጠንና አይነት መጨመር በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም