በጣና ንኡስ ተፋሰስ ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ጥበቃና ልማት ስራ ማከናወን የሚያስችል መረጃ የመቀመርና የማደራጀት ስራ እየተከናወነ ነው

143

ነሐሴ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)በጣና ንኡስ ተፋሰስ ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ጥበቃና ልማት ስራ ማከናወን የሚያስችል መረጃ የመቀመርና የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን 'ዎርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት' የኢትዮጵያ ቢሮ ገለጸ።

'ዎርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት' ዓለም ዓቀፍ የተፋሰስ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ አተኩሮ የሚሰራ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ በኢትዮጵያ ስራውን ከጀመረ ጥቂት ጊዜ ቢሆንም እስካሁን በተፋሰስ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ያከናወነ ሲሆን አሁን ደግሞ በጣና ንኡስ ተፋሰስ ላይ እየሰራ ይገኛል።

የ'ዎርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት' የኢትዮጵያ ቢሮ ጥናትና አካታችነት ባለሙያ አቶ ሙሉነህ ቢምረው የጣና ንኡስ ተፋሰስ በርካታ ጠቀሜታ ያለው አካባቢ መሆኑን ያብራራሉ።

ንኡስ ተፋሰሱ ወደ 3 ሚሊየን ገደማ ዜጎች የሚኖርበት እንዲሁም በርካታ የልማት ስራዎች የሚከናወኑበት አካባቢ ስለመሆኑም ይገልፃሉ።

የዓባይ ተፋስስ አካል የሆነው ጣና ንኡስ ተፋሰስ ሰፋፊ የልማት ስራዎች የሚሰሩበት የልማት ኮሪደር፣የተለያዩ የመስኖ ስራዎች የሚሰሩበት፣ የጣና በለስ ሀይል ማመንጫ ያለበት እንዲሁም ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ያለበት ስፍራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ይህንን መነሻ በማድረግ በንኡስ ተፋሰሱ ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ጥበቃና ልማት ስራ ማከናወን ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል።

በዚሁ የተቀናጀ ስራ ውስጥ የሚካተቱት በውኃ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት፣ የግብርናና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ 'ዎርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት' በአማራ ክልል በሰሜን ሜጫ፣ፋርጣና ደራ ወረዳዎች መረጃ የመቀመርና የማደራጀት እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስራ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

መረጃ የመቀመርና የማደራጀት ስራው ሲጠናቀቅ በንኡስ ተፋሰሱ ዘላቂ የውኃ አጠቃቀምና ንጽህና እንዲኖር ያስችላል ባይ ናቸው።

ለሰርቶ ማሳያነትም በሰሜን ሜጫ ወረዳ ቆጋ የመስኖ ልማት አካባቢ የአፈርና አካባቢ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በጥቅሉ በንኡስ ተፋሰሱ በአካባቢው ያለውን የውኃ መጠን መጨመር ስራዎችን ማዕከል ያደረገ መሆኑንም አቶ ሙለነህ አክለዋል።

የግድቦች በደለል መሞላትን መቀነስ እንዲሁም የአፈር መከላትን መቀነስ የሚቻልባቸውን መንገዶች በተግባር ማሳየት ያለመ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም