በአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ማካለል ላይ በሁለቱ ወገኖች የተደረሰ ስምምነት ላይ ህዝባዊ ውይይት ተካሄደ

159

ነሃሴ10/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የአስተዳደር ወሰን ማካለል ላይ በሁለቱ ወገኖች የተደረሰ ስምምነት ላይ ህዝባዊ ውይይት ተካሄደ፡፡

በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፤ አገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ የተደረሰው ስምምነት የህዝቦችን አንድነትና አብሮ ማደግ በሚያጠናክርና መልኩ እንዲተገበር ማድረግ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የአስተዳደር ወሰን ባለመኖሩ ምክንያት በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ሲነሳ ቆይቷል፡፡

በተለይ መሰረተ ልማት ዝርጋታና ወሳኝ የሆኑ የልማት ስራዎችን ለመስራት እንዲሁም የመሬት ወረራን ጨምሮ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ መቆየቱን ነው የመድረኩ ተሳታፊዎች ያነሱት፡፡

ከተማ አስተዳደሩና ልዩ ዞኑ ተቀናጅተውና ተደጋግፈው በጋራ እንዳያድጉና እንዳይለሙ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱም እንዲሁ፡፡

የአስተዳደር ወሰን ጉዳይን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ከከተማ አስተዳደሩና ከልዩ ዞኑ የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥልቅ ጥናት አካሂዷል ነው የተባለው፡፡

በመድረኩም የጥናቱን መነሻ አድርጎ የተደረሰው ውሳኔ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመድረኩ የተነሱ ዝርዝር ሃሳቦችና የውሳኔ አቅጣጫዎችን በሚመለከት ኢዜአ ዝርዝር ዜና ይዞ የሚቀርብ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም