ኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚያስችል እውቀትና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት ሆናለች- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር

347

ነሐሴ 10 ቀን 2014(ኢዜአ)ኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚያስችል እውቀትና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት መሆኗን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለጸ፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንዳሉት፤አስተዳደሩ የኢትዮጵያን የኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን ከሳይበር ጥቃት በመከላከል የሀገርን ደህንነት እያስጠበቀ ያለ ተቋም ነው፡፡

የሳይበር ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱንና ኢትዮጵያም በ2013 በጀት ዓመት 2 ሺህ 800 የሳይበር ጥቃት እንደተሰነዘረባት አስታውሰው ዘንድሮም ከሶስት እጥፍ በላይ አስተናግዳለች ብለዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል ዘመኑ የደረሰበትን እውቀትና ቴክኖሎጂ በመያዝ እየሰራች ሲሆን፤ የመከላከል አቅሟም የሚያሳየው ይሄንኑ ነው ብለዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት 8 ሺህ 885 የሳይበር ጥቃት ተሞክሮባት 97 በመቶ የሚሆነውን መመከት መቻሏንም ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የሳይበር ጥቃት ምህዳሩ ተገማች ባለመሆኑ በሳይበር ዓለም አስተማማኝ የሚባል የመከላከል አቅም የለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በየዓመቱ የሚጨምረውን የሳይበር ጥቃት ለመመከት የበለጠ መዘጋጀት ግድ ይላል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየደረሰባት ያለው የሳይበር ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ 68ኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ ከዚህ በላይ መዘጋጀት እንዳለባት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ አካላት በጋራ መስራትና ለመከላከል መዘጋጀት አለባቸው ነው ያሉት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ሀሳብ አመንጭነት ከ14 ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚያስችል አገራዊ አቅም ተገንብቶበታል።