የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የልህቀት ማዕከል በመሆን ጠንካራ፣ ተወዳዳሪና የላቀ ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ማፍራት አለባቸው- አቶ ደመቀ መኮንን

170

ነሃሴ 10/2014/ኢዜአ/ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የልህቀት ማዕከል በመሆን ጠንካራ፣ ተወዳዳሪና የላቀ ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ማፍራት አለባቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሁለተኛው ብሔራዊ የሥራ ጉባኤን በማስመልከት በ2014 በጀት አመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ኢንተርፕራይዞችና የዘርፉ አስፈፃሚ ተቋማት እውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር አካሒዷል።

በእውቅና መርሐ ግብሩ የተካሄደው በዘርፉ ጥሩ አፈጻጸም ላስመዘገቡ 61 የማዕከል አገልግሎት ጣቢያዎች፣ ለ138 ወደ መካከለኛ ደረጃ ለተሻገሩ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ለ12 ተቋማት እና የሥራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ መንግስት ለዜጎች ዘላቂ የስራ ዕድል ለመፍጠር በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዜጎችን የኑሮ ውድነት ጫና ማቃለልና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን የመፍታት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

እውቅና እና ሽልማት የተሰጣቸው ወጣቶች የተለያዩ ፈተናዎችን በመቋቋም ከራሳቸው አልፈው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በተሻለ ሁኔታ እንዲቀጥል በማድረግ ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የልህቀት ማዕከላት በመሆን ጠንካራ ተወዳዳሪ እና ክህሎት ያላቸውን ወጣቶች ማፍራት እንዳለባቸውም አስገንዘበዋል።

መንግስት የሥራ ፈጠራና ክህሎት ዘርፍ የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ የጀርባ አጥንት እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈርሃት ካሚል፤ የእውቅና እና ሽልማት መርሐግብሩ በ2014 በጀት አመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ኢንተርፕራይዞችና የዘርፉ አስፈፃሚ ተቋማት የተሰጠ ነው ብለዋል።

የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ አካላት የተሻሉ ስራዎችን እንዲሰሩ ለማድረግና ለዘርፉ ፈፃሚዎችና አስፈፃሚዎች የሞራል ስንቅ እንዲሆን ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው የተሻለ ተነሻሽነት እንዲፈጠር አስተዋፅኦም እንደሚኖረው ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

በዘርፉ ጥሩ አፈጻጸም በማስመዝገብ እውቅና የተሰጣቸው አካላት በበኩላቸው ፤እውቅናው በቀጣይ የተሻሉ አፈፃፀሞችን ለማስመዝገብ ይረዳናል ነው ያሉት።

ለሁለት ቀናት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት የተካሄደው ሁለተኛው ብሔራዊ የሥራ ጉባኤ  ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በመመካከር እና እውቅና በመስጠት ተጠናቋል።