በክልሉ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚሹ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው

134

ሐዋሳ፤ ነሐሴ 10/2014 (ኢዜአ)፡ በደቡብ ክልል በዝናብ እጥረት ሳቢያ በተከሰተው ድርቅ  አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚሹ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ  ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ  እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ ፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋምአ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የበልግ ወቅት ዝናብ እጥረት በተደጋጋሚ ጊዜ ተከስቷል፡፡

በዚህ ሳቢያ ያጋጠመውን የምርት እጥረት ለማካካስ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሎ ከአርሶ አደሩ አቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ አስፈልጓል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ እንዳሉት በተለይ በጎፋ፣ ደቡብ ኦሞና ኮንሶ ዞኖች፤ በደራሼ፣ አሌ፣ አማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች እንዲሁም በጋሞ፣ ወላይታ፣ ጉራጌና ስልጤ ቆላማ ወረዳዎች  ባጋጠመው የበልግ የዝናብ እጥረት በሰብል ከተሸፈነው የእርሻ ማሳ ውስጥ 32 በመቶው በሙሉ ሲወድም 36 በመቶው ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

በዚህም ምክንያት ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ  እንዲሁም ከ716 ሺህ የሚበልጡት  ደግሞ የቅርብ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው በክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት ተገምግሞ መረጋገጡን ተናግረዋል።

በመሆኑም ለእነዚህ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግም ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች የሚከናወኑ ተግባራት ተለይተው እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

በዞን ደረጃ ቀበሌ ከቀበሌ፣ ወረዳ ከወረዳ እንዲሆም ዞን ከዞን የእርስ በርስ የመደጋገፍ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡ ለጋሞ፣ ጎፋና ኮንሶ ዞኖች ድጋፍ መድረጉን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ካለው መጠባበቂያ ክምችት 20 ሺህ ኩንታል ያህል በቆሎን ጨምሮ ሌሎች የምግብ አይነቶች ወደ አካባቢዎች ማጓጓዝ መጀመሩን ግልጸዋል።

በፌዴራል ደረጃ ለ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ እንዲቀርብ  ጥያቄ ቀርቦ ድጋፉን ለሚሹ ወገኖች የማቅረብ ስራው መጀመሩን  ተናግረዋል ፡፡

በበልግ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ የክልሉ መንግስት 55 ሚሊዮን ብር መድቦ  የማካካሻ ዘር እያቀረበ መሆኑን  ኮሚሽነር  ጋንታ ገልጸው፤ እስካሁን በችግሩ ምክንያት በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱንም አስረድተዋል ፡፡

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌትነት በጋሻው በበኩላቸው በዞኑ ዛላ፣ኡባ ደብረፀሐይ፣ ዴምባ ጎፋና፣ ሳውላ ዙሪያና ኦይዳ ወረዳዎች በአጋጠመው የዝናብ እጥረት ሳቢያ  233 ሺህ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።

”አሁንም ቢሆን አካባቢዎቹ ለመኸር ሰብል የሚሆን በቂ ዝናብ እያገኙ አይደለም” ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ አርሶ አደሩ በአካባቢው ያሉትን  የውሃ አማራጭች አሟጦ በመጠቀም ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲያለማ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

የጎፋ ዞንና የአካባቢው ተወላጆች በዞኑ ዛላ እና ኡባ ደብረፀሐይ ወረዳዎች ያለውን የህብረተሰቡን ችግር ተዘዋውረው መመልከታቸውን የጎፋ ዕድገትና ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ አባላቱንና ሌሎች የአካባቢውን ተወላጆች በማስተባበርም በዞኑ አስቸኳይ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች 14 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።