በባሌ ዞን ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች 520 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ

94

ጎባ፣ ነሃሴ 10/2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ጦር ጉዳተኞች ማህበር በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች 520 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።

የምግብ እህል ድጋፉን በቦታው በመገኘት ያስረከቡት የማህበሩ ኃላፊ ኮሎኔል አህመድ በያን ናቸው።

ኮሎኔል አህመድ በወቅቱ እንዳስታወቁት፤ ድጋፉ የኢትዮጵያች በችግር ወቅት የመረዳዳት ባህል አካል ነው ብለዋል።

“ከዝናብ እጥረትና ከወሰን ግጭት ጋር በተያያዘ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖቻችን ለመድረስ ከተለያዩ አካላት በማሰባሰብ ድጋፍ አድርገናል፤ድጋፉንም እናስቀጥላለን” ብለዋል፡፡

የባሌ ዞን ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ከበደ በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤በድርቅና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተደረገውን ድጋፍ ሳይጨምር 600 ኩንታል ሩዝ፣ 60 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት፣ ለጊዜዊ መጠለያ የሚሆን ሸራና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በመንግሥትና በህዝብ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

አቶ ወንድማገኝ እንዳሉት መንግስት በወሰን ግጭት ምክንያት ከጉራ ዳሞሌ ተፈናቅለው በደሎ መና ከሌ ጎልባ ጊዜያዊ መጠለያ የተጠለሉ ከ1ሺህ 273 አባወራዎች ወደ ቄያቸው ለመመለስ የኦሮሚያና ሱማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እየመከሩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ካጋጠመው የድርቅና ሌሎች ሰው ሰራሽ ችግሮች ስፋት አንጻር እየደረሰ ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ሌሎች ወገኖችም ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በድጋፍ አሰጣጡ ሥነሥርዓቱ ላይ ከተገኙት የአካባቢው ሽማግሌዎች መካከል አቶ ማማ አህመዲን በሰጡት አስተያየት፤ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ ከዚህ ችግር እስኪላቀቁ ድረስ ሁሉም ወገን እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

በባሌ ዞን ስድስት ወረዳዎች ውስጥ 400 ሺህ የሚጠገ ህዝብ በዝናብ እጥረት ምክንያት ለድርቅ ተጋላጭ መሆኑ ከቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የባሌ ዞን ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡