ኢዜአ እና ኦቪድ ግሩፕ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

142

ነሃሴ 10/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ እና ኦቪድ ግሩፕ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

የመግባቢያ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እና የኦቪድ ግሩፕ ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ ተፈራርመዋል።

የኦቪድ ግሩፕ ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ፤ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኦቪድ ግሩፕ በተለይም በግንባታ ዘርፍ በኢትዮጵያ አዲስ ቴክኖሎጂ በማስተዋወቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሥራ መስራቱን አንስተዋል።

ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን በ18 ወራት ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ገንብቶ ማስረከብ መቻሉን ለአብነት የጠቀሱት ሥራ አስፈጻሚው በዘርፉ ግንባታው ዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራርን ይዞ ብቅ ማለቱን ገልጸዋል።

ለአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር 200 ቤቶችን የያዙ አራት ሕንጻዎችን በሦስት ወራት ገንብተው በማጠናቀቅም ለአገልግሎት እንዲበቁ መደረጉን ተናግረዋል።

ኦቪድ ግሩፕ በሕዝቡ ዘንድ የሚታይና ተጨባጭ ውጤት ማሳየት በመፈለጉ እስካሁን የማስታወቂያ ሥራ አልሰራም ብለዋል።

በቀጣይ ግን ኩባንያውን የበለጠ ለማስተዋወቅና እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ለዘርፉ እድገት የሚኖረውን አስተዋጽኦ ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ ከኢዜአ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል።

”ከዚህ አንጋፋ ተቋም ጋር መሥራት ትልቅ ደስታን የሚፈጥር ነው” ያሉት አቶ ዮናስ የትብብር ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን እውቀትና ልምድ በመጋራት አገር መጥቀም የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ኩባንያው ያለፈበትን ሁኔታ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም በኢዜአ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ በኢትዮጵያ ሥር ሰዶ የቆየውን የግንባታ ችግር ለማቃለል ኦቪድ ግሩፕ የጀመረው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራን ማጠናቀቅ እንደሚቻል በተግባር ያሳየና አዲስ የሥራ ባህል ይዞ የመጣ ኩባንያ በመሆኑ ለአገር ልማት የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በመሆኑም ኢዜአ ከእንዲህ አይነት ተቋማት ጋር አብሮ መሥራቱ ለአገር ልማትና ጠንካራ የሥራ ባህል ለማዳበር ለሚደረገው ጥረት አጋዥ ይሆናል ነው ያሉት።

በመሆኑም በስምምነቱ መሰረት ኦቪድ ግሩፕ ለአገር እያበረከተ ያለውን እንቅስቃሴ እና የኩባንያውን የኮሙኒኬሽን ሥራዎች በማስተዋወቅ ኢዜአ በስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ኢዜአ ከዚህ ቀደምም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን የተለያዩ ስምምነቶች መፈራረሙ ይታወሳል።