የተደረገልን የቤት እድሳት ያለብንን ስጋት አቃሎ አዲስ ህይወት ለመጀመር አስችሎናል- ነዋሪዎች

139

ነሃሴ 10/2014/ኢዜአ/ የተደረገላቸው የቤት እድሳት ያለባቸውን ስጋት አቃሎ አዲስ ህይወት ለመጀመር እንዳስቻላቸው በአዲስ አበባ  የቤት እድሳት ተጠቃሚ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

“ከዘጠኝ ልጆቼ ጋር በላስቲክ ቤት የኖርኩት አስቸጋሪ ሕይወት ተቀይሮ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ጀምሬያለሁ”- የሚሉት የቤት እድሳት የተደረገላቸው እናት ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ጌጃ ሰፈር ለአራት ዓመታት ዘጠኝ ህፃናት ልጆቻቸውን ይዘው የኖሩበት ጊዜ በእጅጉ ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳሉ ወይዘሮ ለምለም ተስፋዬ።

በላስቲክ በተሸፋፈነችው ደሳሳ ቤታቸው በነበረው የሕይወት ልምዳቸው “መሽቶ መንጋት እንዲሁ ቀላል አልነበረም” ይላሉ።

በጎዳና ላይ ከመኖር በማይተናነሰው የሕይወት ውጣ-ውረድ ከዝናብና ብርዱ እንዲሁም የጠራራው ፀሐይ ወበቅ በተጨማሪ ብዙ ፈታኝ ነገሮችን እንዳለፉ ይናገራሉ።

በላስቲክ በተጠጋገነችው ቤቴ መሽቶ በጊዜ መተኛት የማይታሰብ ነበር የሚሉት ወይዘሮ ለምለም ዘጠኝ ሴት ልጆቼን ከዝናብና ብርድ ከመከላከል በተጨማሪ ሌሊቱ እስከሚጋመስ በስካር ከሚንገዳገድና ለጥፋት ከሚንቀሳቀስ ቤትና ልጆቻቸውን የመጠበቁ ኃላፊነት ቁጭ አድርጎ ያሳድራቸዋል።

ሌሊቱ ተገባዶ ሲነጋም ለወይዘሮ ለምለም የቤተሰብ ኃላፊነት ቀጥሎ የሚውል በመሆኑ የአራት ዓመታት የጌጃ ሰፈር ሕይወታቸው እንደፈተናቸው ይናገራሉ።

በብዙ ችግርም ቢሆን በአሸናፊነት አልፎ ለተሻለ ሕይወት መብቃት መቻል ደግሞ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መሆኑን ይገልጻሉ።

አሁን ላይ ወይዘሮ ለምለምና ልጆቻቸው በተሻለ ቤት ውስጥ በመኖር በአዲስ የሕይወት ምዕራፍ መኖር ጀምረናል ይላሉ።

ለዚህ የበቁት ደግሞ በመንግሥት አስተባባሪነት ባለሀብቶች፣ ወጣቶች፣ አጠቃላይ ማኅበረሰቡና ግለሰቦች በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን እየመሩ ላሉ ዜጎች እየተደረገ ባለው የበጎፈቃድ አገልግሎት በመሆኑ እርሳቸውም እድለኛ በመሆናቸው አመስግነዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 12 የቤተሰብ አባላትን ይዘው በደሳሳ ጎጆ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት አቶ ደረጄ ትርፌ፤ የቤት እድሳት ስለተደረገላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ከእድሳቱ በፊት በተለይም በክረምቱ የሚወርደው ዝናብ ቤታቸው ውስጥ ያንጠባጥብ ስለነበር ተኝቶ ለማደር አስቸጋሪ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ለረዥም ዓመታት የቀን ሥራ በመሥራት ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ የነበሩት አባወራው ከእለት ጉርስ ያለፈ ገንዘብ ስለሌላቸው ማደስ ባለመቻላቸው በርካታ አስቸጋሪ ወቅቶችን ማሳለፋቸውን ይናገራሉ።

በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቶችን በማሳተፍ ቤታቸው ታድሶ ከጎርፍና ዝናብ ስጋት ተላቀው እየኖሩ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በልደታ ክፍለ ከተማ አራት ልጆችን ይዘው ለሰው ልጅ ኑሮ በማይመች አካባቢ ረዥም ዓመታትን በችግር መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ክንፈ ምህረት፤ ዛሬ ላይ አዲስ ሕይወት ጀምሬያለሁ ይላሉ።

”በታደሰ ቤቴ ልጆቼን በአንድ ጣሪያ ሰብስቤ ጥሩ ሕይወት እንድመራ ላደረጉኝ መልካም አሳቢዎችና አድራጊዎች አመሰግናለሁ” ብለዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ራህመት መርጋ፤ ቤታቸው ፈርሶ በመሰራቱ መላው ቤተሰቡን ያስደሰተ መልካም አጋጣሚ መሆኑን በመግለጽ ለተደረገላቸው ሁሉ አመስግነዋል።

በአዲስ አበባ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ከቤት እድሳት በተጨማሪ በሰብአዊና ማሕበራዊ አገልግሎት፣ የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ የትራፊክ ቁጥጥርና ሌሎችም በመከናወን ላይ ይገኛሉ።