በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ2 ሺህ 500 በላይ የአቅመ ደካማ እናቶች ቤቶች ግንባታና እድሳት ተከናውኗል

266

አዳማ፤ ነሐሴ 09/2014 (ኢዜአ)፡ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ2 ሺህ 500 በላይ የአቅመ ደካማ እናቶች ቤቶች ግንባታና እድሳት መከናወኑን የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ ገለጹ። 

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት በአዳማ ከተማ  በሊጉ የሴቶች አደረጃጀት እየተከናወኑ ያሉ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራትንና የከተማ ግብርና የስራ እንቅስቃሴን ዛሬ ጎብኝተዋል።

የሊጉ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የከተማ ግብርና የነዋሪዎችን የምግብ ፍጆታ ለመደጎምና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በአዳማ ከተማ የአቅመ ደካማ እናቶችን ቤት በመገንባትና በማደስ በተሰራው ሥራ የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪና ለሌሎች ከተሞች ጭምር ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

የክረምት በጎ ፍቃድና የዜግነት አገልግሎት በሊጉ አደረጃጀት ብቻ ከ2 ሺህ 500 በላይ ቤቶችን በአዲስ ለመገንባትና ለማደስ የተያዘው እቅድ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በተለይ አቅመ ደካማ እናቶች ላይ ትኩረት ያደረግው ሥራ  በከተማዋ የሴቶች አደረጃጀት ብቻ መከናወኑ ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑንም አመልክተዋል።

“ምግቤን ከጓሮዬ” በሚል መሪ ሀሳብ  በሊጉ ሴት አመራሮች የተጀመረው የከተማ ግብርና እንቅስቃሴ በነዋሪዎች ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

መላውን የሊጉን አመራሮችና አባላትን ያቀፈ የከተማ ግብርና ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህም አብዛኞቹ እናቶች የዕለት የምግብ ፍጆታቸውን ከመደጎም ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ገቢ እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዳማ ከተማ የሴቶች ሊግ ሃላፊ ወይዘሮ በሪራ ዑስማ በበኩላቸው በከተማዋ በሴቶች ሊግ አደረጃጀት ብቻ 64  የአቅመ ደካማ እናቶች ቤቶት ግንባታና እድሳት መከናወኑን ገልጸዋል።

በዚህም በስድስቱ ክፍለ ከተሞችና በ18ቱ የከተማዋ ቀበሌዎች ያሉ የሊጉ አመራሮችና አባላት ህዝቡን በማስተባበር የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበርም አመልክተዋል።

 በቀበሌያቸው 18 የአቅመ ደካማ እናቶች ቤት እድሳትና ግንባታ በማጠናቀቅ ማስረከባቸውን የገለጹት ደግሞ የአዳማ ከተማ አባ ገዳ ክፍለ ከተማ የኦዳ ቀበሌ ሊቀመንበር ወይዘሮ ፎዝያ ኢብራሂም ናቸው።

ከተጠናቀቁት ውስጥም 12 የሚሆኑት አዲስ የተገነቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ በከተማ ግብርና የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።

አዲስ ቤት ከተገነባላቸው የቀበሌው ነዋሪ መካከል ወይዘሮ ተዋበች ጫካ እንደገለጹት መኖሪያ ቤታቸው በማርጀቱ ምክንያት በተለይም በክረምት ወቅት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የቀበሌው ሴቶች አሮጌውን ቤታቸውን አፍርሰው አዲስ ቤት ገንብተው እንደሰጧቸው ተናግረዋል።

“በዚህም መስተደድሩንና ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ” ነው ያሉት።