በማዕከላዊ ጎንደር የወባ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ፈጣን ምላሽ ሰጪ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው

89

ጎንደር፤ ነሐሴ 9/2014(ኢዜአ) ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ከ400 በሚበልጡ የጤና ተቋማት ፈጣን ምላሽ ሰጪ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

ባለፈው ወር በዞኑ ሶስት  ወረዳዎች ተቀስቅሶ የነበረው የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በተደረገ ርብርብ 27ሺህ የነበረውን ሳምንታዊ የወባ ተጠቂዎች ቁጥር ወደ 7ሺ ዝቅ ማድረግ እንደተቻለ ተመልክቷል።

የጤና ባለሙያዎችንና የየአካባቢውን አስተዳደር ያካተተው ግብረ ሃይሉ ከሀምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ  የቤት ለቤት ቅኝትና አሰሳ በማድረግ የወባ በሽታ ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች በጤና ተቋማት ምርመራ እየተደረገላቸው መሆኑን መምሪያው ገልጿል።

የመምሪያው ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ምሳ ታረቀኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  ማህበረሰቡ በወባ በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ስራው ተገቢውን ግንዛቤ እንዲያገኝ የቅስቀሳ ስራ በማከናወን ግብረ ሃይሉ ሰፊ የንቅናቄ ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡

የክረምት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር የወባ ትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን በዘመቻ የማፋሰስና የማዳፈን ተግባራት በማከናወን ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አሰረድተዋል።

በጤና ተቋማቱ በቂ የወባ መድሃኒትና የጤና ባለሙያዎች እንዲሟላ ከማድረግ ሌላ  50ሺህ የሚጠጋ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ስርጭት መከናወኑን ጠቅሰዋል።  

የመምሪያው ምክትል ሃላፊ እንዳሉት፤ የወባ ተጋላጭ በሆኑ 20 ቀበሌዎችም ከ22ሺህ በሚበልጡ መኖሪያ ቤቶች የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል፡፡

ባለፈው ወር በጎንደር ዙሪያ ፣ምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ ወረዳዎች የተቀሰቀውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በተደረገ ርብርብ 27ሺህ የነበረውን ሳምንታዊ የወባ ተጠቂዎች ቁጥር ወደ 7ሺ ዝቅ ማድረግ እንደተቻለም አመልክተዋል።

በቅርቡ በተከሰተ የጎርፍ መጥለቅላቅ ሳቢያ በወረዳው 11 ቀበሌዎች የወባ ወረርሽኝ ስጋት መኖሩን የጠቆሙት ደግሞ የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወርቅነህ ታከለ ናቸው፡፡

በእነዚህ  ቀበሌዎች የጎርፍ ውሃን የማፋሰስና የማዳፈን ስራ እየተካሄደ መሆኑን  ጠቅሰው፤ 2ሺ 500 የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር መሰራጨቱንም አስረድተዋል፡፡

ቤት ለቤት በተካሄደ አሰሳና ቅኝት ስራ የወባ በሽታ ምልክት የታየባቸው ከአንድ ሺህ በላይ ታማሚዎች ምርመራ ተደርጎላቸው የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም