ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሂደት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል- ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል

869

አዲስ አበባ ነሃሴ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ)  ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሂደት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለፁ።

ሁለተኛው  ብሔራዊ የሥራ ጉባኤ  “ዘላቂ ሥራ ለብሩህ ነገ” በሚል መሪ ሃሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፤ ጉባዔው ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት ለልምድ ልውውጥ እና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች የሚቀርቡበት መሆኑን ገልጸዋል።

በተግባር አፈጻጸም ሂደት ያሉ መልካም ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች ተለይተው የሚወጡበትና ለቀጣይ ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ምቹ መደላደል ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

የምክክር መድረኮች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የጎላ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሂደት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤ በጉባዔው ለሥራ አጥነት ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት በማድረግ የመፍትሔ ሃሳብ የሚቀመጥበት መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩም ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በጥናቱ የተገኙ ውጤቶችና ምክረ-ሃሳቦች ወደ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ አሰራሮችና አደረጃጀቶች እንዲያመሩ ይደረጋል ብለዋል።

በመድረኩ  በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ እጩ የፒ.ኤች.ዲ ተማሪ ሙሉጌታ በቀለ፤ በኢትዮጵያ የግብርና ሥራ ስምሪት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መካከል ያለውን ትስስር በሚመለከት ጽሑፍ አቅርበዋል።

ብሔራዊ የሥራ ጉባዔ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው መንግሥት ሥራ ፈጠራን አስመልክቶ ያሰቀመጠውን ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ተከትሎ በቀድሞ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ2019 ነበር የተጀመረው።