ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን በተሻለ መልኩ ማስኬድ የሚያስችለውን ሥራ እያከናወነ መሆኑ ገለጸ

92

ነሐሴ 9 ቀን 2014(ኢዜአ) ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን በተሻለ መልኩ ማስኬድ የሚያስችለውን ሥራ እያከናወነ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ከ13 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አበበ ግርማ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ትውልድ ከሚባሉትና በዘመናዊ መልክ ከተደራጁት ውስጥ አንዱ ነው።

ነገር ግን አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ወደ አካባቢው በገባበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው ለአሥር ዓመታት ያካበተው ሃብት ላይ ዘረፋና ውድመት እንደደረሰበት አስታውሰዋል።

ቡድኑ አካባቢውን ለቆ ከወጣ በኋላ ግን በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት በተደረገ ድጋፍ ዩኒቨርሲቲውን በተወሰነ መልኩ ማደራጀት መቻሉን አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው ከመጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን ቀጥሏል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅትም በተለይ የቤተ-ሙከራዎችና ሌሎች የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚደግፉ ቁሳቁሶች በተሻለ መንገድ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው መልሶ እንዲደራጅና ትውልድ የመቅረጽ ሥራውን በተሻለ መልኩ እንዲያከናውንም ዘርፈ- ብዙ ሥራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ አካላት ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው የገለጹት።

ዩኒቨርሲቲው ከበፊቱ በተሻለ መንገድ የመማር ማስተማር ሥራውን ማካሄድ እንዲችል በሚደረገው ጥረት ሁሉም አካላት ሊሰራ እንደሚገባም በመጠቆም።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በቆየበት ወቅት የተማሪ መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-ሙከራዎች፣ መኝታ ክፍሎችና አጠቃላይ አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ዘርፏል።

ቡድኑ በዘረፋ መውሰድ የማይችላቸውን ንብረቶች ደግሞ በማውደም በአጠቃላይ የመማር ማስተማር ሥራውን ማከናወን የማይችልበት ደረጃ እንዲደርስ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም