በከተሞች የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ተከናውነዋል - ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ

አዳማ ነሐሴ 09/2014(ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት አመት በከተሞች የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች መከናወኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ አስታወቁ።

የሴክተሩ የ2014 በጀት ዓመት የስራ እቅድ አፈፃፀም ግምገማና  የአዲሱ በጀት አመት ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የከተማ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ዓመታዊ የጋራ ጉባኤ በአዳማ እየተካሄደ ነው ።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለፁት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ተቋማዊ ሪፎርምና ለውጥ መሰረተ ባደረገ መልኩ ምቹ የስራ ድባብ መፍጠር ተችሏል።

በተለይ በጦርነት የተጎዱ ከተሞች መሰረተ ልማት ጥገናና አገልግሎት ማስጀመር፣ ክልሎችን ትርጉም ባለው መልኩ ከመደገፍ አንፃር የተሻሉ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

ለነዋሪዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ቁልፍ ሚና ያላቸው የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በከተሞች ከድህነት ወለል በታች ያሉ ዜጎች በሴፊቲኔት ፕሮግራም እንዲሰማሩና ሰርተው ገቢ እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።

የከተማ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ነባሩን የቤት ልማት ፕሮግራሞችን በመፈተሽና በመከለስ አልሚዎች በስፋት እንዲሰማሩ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ለመንግሥት መቅረቡን ተናግረዋል ።

በፅዳትና ውበት፣ የአረንጓዴ ፓርኮች ግንባታ፣ ጅምር ተስፋ ሰጪ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል ።

የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን ከማዘመን አንፃር መሻሻሎች ቢኖሩም ነዋሪዎችን የሚመጥን አገልግሎት ከመስጠት አኳያ አሁንም ሰፊ ክፍተቶች  መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

"የአገልግሎት ዘርፍን በዲጂታል ቴክኖሎጂ መምራትና አሁን የሚታየውን የተገልጋዩን እንግልት ከማስቀረት አንፃር ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል" ብለዋል።

የከተሞች የማዘጋጃ ቤት ገቢ ማሻሻልና የገቢ አማራጮችን ማስፋት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት መንግሥትና አልሚዎችን በማሳተፍ መቅረፍ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በመጠን፣ በጥራትና ደረጃዎችን ማሻሻል የአዲሱ በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በተለመደው አሰራር ተጉዘን ከተሞቻችን መለወጥ አንችልም" ያሉት ወይዘሮ ጫልቱ "አዳዲስ አሰራሮችና እንሼቲቮችን መቅረፅና ተግባራዊ ማድረግ የቀጣይ ዓመት የጋራ ስራችን ነው" ሲሉ አመላክተዋል ።

"ዲጂታል አገልግሎቶች ማስፋፋትና አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የፕሮጄክቶች ግንባታ ደረጃዎችና አስተዳደር  ማሻሻልና በአዳዲስ ቴክኖሎጂና አሰራር መደገፍ አለብን" ያሉት ሚኒስትሯ፣ "ለዚህም የዝግጅት ምዕራፍ በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን " ብለዋል ።

በክልሎች ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ድሬዳዋ፣ አማራና ሲዳማ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው መሆኑን የገለፁት ደግሞ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አማካሪና የ2014 ዓ.ም የሴክተሩን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ ወልደሚካኤል ናቸው።

በተለይ የከተሞችን ገቢ ከማሳደግ፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሻሻሎች የታየባቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም