የሳርቤት - ጎፋ ማዞርያ - የፑሽኪን ጎተራ መንገድ ግንባታ ክንውን በፈተናም ውስጥ ሆነን የላቀ ልማት ማስመዝገባችንን ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

171

ነሐሴ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሳርቤት - ጎፋ ማዞርያ - የፑሽኪን ጎተራ መንገድ ግንባታ ክንውን በፈተናም ውስጥ ሆነን የላቀ ልማት ማስመዝገባችንን የሚያመላክት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የሳርቤት - ጎፋ ማዞርያ - የፑሽኪን ጎተራ ማሳለጫ ዘመናዊ የመንገድ ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት ተመረቋል።

በመንገድ ፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የመንገዱ ግንባታ መጠናቀቅ በፈተናም ውስጥ ሆነን የላቀ የልማት ክንውን ማስመዝገባችንን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው በጀት ዓመት 24 አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ማጠናቀቁን ገልጸው፣ ተጨማሪ የመንገድ ጥገና መከናወኑንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ከ282 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የሳርቤት - ጎፋ ማዞርያ - የፑሽኪን ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ፕሮጀክት መጠናቀቅም ለአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ገጽታ ግንባታና ዘመናዊ አገልገሎት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንገዱ ግንባታ በላቀ ቴክኖሎጂ፣ በውበት፣ በጥራትና በተሻለ ጥራት የተከናወነ ስለመሆኑም ከንቲባዋ ጠቅሰዋል።

ለየመንገዱ ግንባታ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪ ችግር ለመፍታት ከምንጊዜውም በላይ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም