በአዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች በብዛት ወንጀል የሚፈፅሙት የውጭ አገር ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ ናቸው

315

ነሐሴ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች በብዛት ወንጀል የሚፈፅሙት የውጭ አገር ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ገለጸ።

የስደትና ስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ በስደት የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ጉዳይ በጥንቃቄ ካልተመራ ለወንጀል ድርጊቶች እየከፈተ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የስደተኝነት እውቅና የተሰጣችው፣ በሕገ ወጥ መልኩ የገቡና በሕጋዊ መንገድ ገብተው የቆይታ ቪዛ ፈቃዳቸው የተቃጠለባቸው የውጭ አገር ዜጎች እንዳሉ ይታወቃል ።

ከእነዚሁ ስደተኞች መካከል በሽብር፣ የሕገ ወጥ ገንዘብና የሰዎች ዝውውርና ሌሎችም የወንጀል ድርጊቶች ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ስደተኞች የሚኖሩት በተለይ ጠረፋማ አካባቢዎች በመሆኑ ከጎረቤት አገራት ነባራዊ ሁኔታና ከድንበር ቁጥጥር መላላት ጋር ተያይዞ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ይሕንን ለመከላከልም አገልግሎቱ ከክልልና ከፌዴራል ጸጥታ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በየትኛውም ሁኔታ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵየ ቆይታችው የአገሪቷን ህግ አክብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።

በዚህ ረገድ አገልግሎቱ ስደተኞቹ ባላቸው አደረጃጀት መሰረት የኢትዮጵያን ሕግና ስርዓት የማሳወቅ ተግባሩን የሚያከናውን ሲሆን ከሕግ የሚያፈነግጡ ተጠያቂ ይደረጋሉ ብለዋል።

በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ ሕገ ወጥና ሀሰተኛ ሰነዶች የሚያዘጋጁ የውጭ ዜጎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ነገር ግን ሁሉም ወንጀሎች የሚፈጽሙት በስደተኞቹ ብቻ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በእስካሁኑ ሂደት በአዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች በብዛት ወንጀል የሚፈፅሙት የውጭ አገር ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የትኛውም ግለሰብ ስደተኛ የሚባለው ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጥገኝነት ጠይቆ ምክንያቱ አሳማኝ ሆኖ ከተገኘ የጥገኝነት ወይም የስደተኝነት ዕውቅና ከተሰጠው ብቻ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢሚግሬሸና ዜግነት አገልግሎት በኩል የውጭ ዜጎች ብዛት፣ አይነትና ስምሪት ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በቅርቡም በሶስቱም ምድብ የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎችን ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን አስታውሰው፤ በእስካሁኑ ሂደትም በስደተኝነት ዕውቅና የተሰጣችው ዜጎች በብዛት እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ምዝገባው በሀገር ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ዜጎችን ህጋዊ ለማድረግ ያለመ እንጂ በመመዝገባቸው ብቻ  የትኛውም አይነት ተዕጽኖ አይደርስባቸውም ብለዋል።

በሌላ በኩል ሁሉም የቀጣናው አገራት ስደተኞች ስለሚጋሩ ዜጎችን ለስደት የሚዳርጉ ምክንያቶችን  ከምንጩ ለማድረቅ በጋራ መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ በሰጠው መግለጫ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ምዝገባ  ከ36 የተለያዩ አገራት የመጡ ከ70 ሺህ በላይ የውጭ ዜጎች ተመዝግበዋል።

የውጭ ዜጎችን ሕጋዊ የማድረግ ሂደት የተጀመረው ምዝገባም እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም መራዘሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም