ቻይና የኢትዮጵያን የግብርና ሴክተር ለመደገፍና በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ ናት - በቻይና የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል

104

ነሀሴ 9/2014 /ኢዜአ/   ቻይና የኢትዮጵያን የግብርና ሴክተር ለመደገፍና በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ዉ ፔንግ ገለጹ።

በቻይና ሥልጠና ላይ ከሚገኙ ከተለያዩ ከአፍሪካ አገራት ከተውጣጡ ጋዜጠኞች ጋር ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት አስመልክቶ ዳይሬክተር ጀነራል ዉ ፔንግ መግለጫ ሰጥተዋል።  

በመግለጫቸውም፤ የቻይናና የአፍሪካ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1956 ጀምሮ በተለያዩ የልማትና የትብብር መስኮች እየታገዘ አሁን ላይ ጠንካራ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት ግንኙነት በወዳጅነት፣ በፍትሃዊነትና በእኩል የጋራ ተጠቃሚነት መርህን የተከተለ በመሆኑ ያለፉት የትብብር ዓመታት በቂ ማስረጃ ናቸው ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ ከአራት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም (ፎካክ) የቻይና አፍሪካ አጋርነቱን በመጠናከርና ለጋራ ዓላማ በጋራ ለመሰለፍ አስችሏል ነው ያሉት።

ፎረሙም ባስቀመጣቸው አዳዲስ ዘጠኝ የትብብር መስኮች ላይ ባለፉት ዓመታት አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸው በቀጣይም የተሻሉ ውጤቶች ለማስመዝገብ ቻይና ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም ከቻይና ጋር በተለያዩ የትብብር ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት ያላት አገር መሆኗን ተናግረው በተለይም ደግሞ በማኒፋክቸሪንግና፣  በግንባታና በኢንደስትሪ ዘርፎች ላይ ትብብሩ ሰፊ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፏን ለማልማት ከፍተኛ አቅም ያላት አገር መሆኗን ገልጸው በተለይም “የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት” መሆን የሚያስችል ትልቅ እምቅ አቅም እንዳላት ነው እምነታቸውን የገለጹት።

ይህንንም ተከትሎ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በግብርናው ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ጭምር በዘርፉ ለመሳተፍ የሚፈልጉ በርካታ የቻይና ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም