ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ካሉ አገራት ጋር በጋራ ለመበልጸግ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ካሉ አገራት ጋር በጋራ ለመበልጸግ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች

ሐሴ 9/2014 /ኢዜአ/ ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ካሉ አገራት ጋር በጋራ ለመበልጸግ ድጋፏን አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን የቻይና ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኋ ቹዪንግ ተናገሩ።
በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማኅበር ሥር የሚንቀሳቀሰው የቻይና ዓለም አቀፍ የፕረስ ኮሚኒኬሽን ማዕከል የዘንድሮውን ሥልጠና በቻይና-በቤጂንግ በይፋ አስጀምሯል።
ሥልጠናው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከላቲን አሜሪካ 55 አገራት ለተውጣጡ 75 ጋዜጠኞች የሚሰጥ ሲሆን ለቀጣይ ሦስት ወራት እንደሚቆይ ተመልክቷል።
ሥልጠናው በዋናነት ቻይና ከእነዚህ ሦስት አህጉራት ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያ ግንኙነት እንዲሁም የቻይና ታሪክና ባህል በስፋት ይዳስሳልም ነው የተባለው።
ጎን ለጎንም ጋዜጠኞቹ ቻይና አሁን የደረሰችበትን የእድገት ማማ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ተዘዋውረው የመመልከት እድል እንዳላቸው ተጠቅሷል።
የቻይና ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኋ ቹዩንግ፤ “ቻይና በርካታ አገራት የሚያቅፈው በማደግ ላይ ያሉ አገራት ስብስብ ውስጥ አንዷ ናት፤ በዚህም በርካታ ክፉና ደግ ጊዜን አብራ አሳልፋለች” ብለዋል።
“በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ቻይና ሕጋዊ መቀመጫዋን በመንግሥታቱ ድርጅት እንድታገኝ ያደረጉትን አስተዋጽዖ አንረሳውም” ብለዋል።
አሁን ላይ ቻይና የተሻለች አገር ናት ያሉት ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ እነዚህን በማደግ ላይ ያሉትን አገራት ለመርዳትና በጋራ ለመበልጸግ ያላትን ቁርጠኝነት ተናግረዋል።
በጥረትና በትጋት የጋራ ልማት ለማምጣት እንሰራለን፤ ሌሎች አገራት የራሳቸውን የልማት መስመር በመከተልና የተሻለ የኑሮ ደረጃ ሊኖራቸው ይገባልም ነው ያሉት።
ቻይና ለማሳካት በምታደርገው የጋራ በልጽግና ግስጋሴ ውስጥ አንድም ቻይናዊ ዜጋ ሳይጠቀም መቅረት የለበትም ብላ እንደምታስብ ሁሉ በታላቁ የጋራ ልማት አጀንዳ ውስጥም አንድም አገር ወደ ኋላ መቅረት የለበትም ብላ ታምናለች በማለት የቻይናን አቋም ገልጸዋል።
እኛ በማደግ ላይ ያለነው አገራት የጋራ አጀንዳ ያለን አገራት ነን፤ ልባችንም የተቀራረረበ ነው በማለት የተናገሩት ሃላፊዋ በአሁኑ ወቅት ዓለም በርካታ ፈተናዎች እየተጋፈጠች በመሆኑ እነዚህን ፈተናዎች በትብብርና በአንድነት መንፈስ መመከት ይገባል ብለዋል።
አሁን ላይ በዓለም ላይ በርካታ ኢ-ፍትሃዊ ነገሮች እየተፈጸሙ መሆኑን ጠቅሰው ጥቅሞቻችንን ለማስከበር በጋራ መቆም አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ጫናዎችና የተሳሳቱ ፕሮፓጋንዳዎች መኖራቸውን በመገንዘብ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ቻይናንም ጨምሮ በአንድ ድምጽ መናገር አለባቸው ብለዋል።