በጎሎል ወንዝ ድልድይ ግንባታ መጓተት በእለት ተለት ኑሯችን ላይ ችግር እየገጠመን ነው-የዳሪሙ ወረዳ ነዋሪዎች

174

መቱ ነሐሴ 8/2014(ኢዜአ) በኢሉ አባቦር ዞን ዳሪሙ ወረዳ በጎሎል ወንዝ ድልድይ ግንባታ መጓተት በእለት ተለት ኑራቸው ላይ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ።

የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ ችግሩ የተፈጠረው ለድልድዩ ግንባታ የሚያስፈልገውን ማሽን ወደ ስፍራው ከማጓጓዝ ጋር ተያይዞ መሆኑን  ገልጾ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ግንባታውን ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አስታውቋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ስናክ ለተባለ የግንባታ ተቋራጭ ድርጅት በ15 ሚሊዮን ብር የተጀመረው  የጎሎል ወንዝ ድልድይ ግንባታ ስራ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃት አለመቻሉ  በአከባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል።

በድልድዩ ግንባታ አለመጠናቀቅ ምክንያት ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጡ መሆናቸውን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ተሽከርካሪዎች ከወንዙ ተሻግረው ስለማይሄዱ ሁሉንም ተግባሮቻቸውን በሰው ጉልበት ለማከናወን መገደዳቸው አስታውቀዋል ።

ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል አቶ ተማም አወል በወንዙ በበጋም ሆነ በክረምት ለመሻገር አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፣ የታመሙ ሰዎችን እንዲሁም ወላድ ሴቶችን በአልጋ ተሸክመው እሩቅ መንገድ ለሕክምና እንደሚጓዙ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ መቸገራቸውንና ለብዙ እንግልትና ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

 ነዋሪዎች በድልድዩ  ግንባታ አለመጠናቀቅ ምክንያት ህክምና ለማግኘት እንዲሁም ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማውጣትና የግብርና ግብአቶች ገዝተው ወደ አካባቢያቸው ለማስገባት  መቸገራቸውን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የቤና አንድ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ መሐመድ ናቸው።

በድልድዩ አለመሰራት ምክንያት ተሽከርካሪዎች ከወንዙ ማዶ ላለው ሕብረተሰብ አገልግሎት መስጠት ስለማይችሉ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን በሸክም ወደ ጤና ተቋማት ለመውሰድ በመገደዳቸው  ለከፋ ችግር እየተጋሉ መሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል ።

ሕመማቸው ፀንቶባቸው ሕክምና ሳያገኙ ለሕልፈት የሚዳረጉ መኖራቸውንም አክለዋል ።

“ድልድዩ ግንባታው ባለመጠናቀቁና ተሽከርካሪዎች ወደ አካባቢያቸው መግባት ባለመቻላቸው ምርታችንን ወደ ገበያ ማውጣት ተቸግረናል” ያሉት ደግሞ አርሶ አደር  ሙስጠፋ አህመድ ናቸው።

ምርታቸውን በሰው ጉልበት አጓጉዘው ገበያ ለማውጣት በሚያደርጉት ሂደት ለአላስፈላጊ ወጭና ድካም እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የሚመለከተው አካል ለድልድዩ ግንባታ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

በኢሉ አባቦር ዞን መንገዶችና ሎጂስቲክስ ጽሕፈት ቤት የኮንትራት አስተዳደር ባለሙያ አቶ ዮናስ ሰለሞን ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ተቋራጩ ለድልድዩ ስራ የሚያስፈልገውን ማሽን ጭኖ ወደ ስፍራው ለመውሰድ ባለመቻሉ ችግሩ ተፈጥሯል።

“ምክንያቱ ደግሞ የመንገድ ምቹ አለመሆን ጋር ተያይዞ የተያያዘ ነው” ብለዋል።

“በምዕራብ ወለጋ በኩል ያለውን አማራጭ መንገድ በመጠቀም ማሽኑን ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው” ሲሉ አመልክተዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጌታሁን ካሳሁን በአዲሱ በጀት ዓመት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ድልድዩ እንዲጠናቀቅና ችግሩ እንዲፈታ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።