በከተማው ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

164

ነሐሴ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ከተማ ከ1 ቢሊዮን 151 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ግንባታቸው ተጀምሮ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
ፕሮጀክቶቹ በመጓተታቸው ምክንያት ከ264 ሚሊዮን ብር በላይ መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸው ተመልክቷል ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተንኳይ ጆክ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በአዲሱ በጀት ዓመት የተጓተቱ ነባር ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ስራ ላይ ለማዋል አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ነው ።

በጋምቤላ ከተማ በ2007 በጀት ዓመት በ1 ቢሊዮን 151 ሚሊዮን ብር የአምስት ቢሮዎች ፣የአንድ የልዩ ኃይል ካምፕ፣የጋምቤላ ስታዲዬምና የአንድ ዘመናዊ የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታ ስራ መጀመሩን አስታውሰዋል።

የፕሮጀክቶቹን ግንባታ በሶስት ዓመት ጊዜ ለማጠናቀቅ ውል ቢገባም እስካሁን ሳይጠናቁ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የክልሉን የበጀት አቅም ባላገናዘበና ባልተጠና መልኩ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ መጀመር ለመጓተቱ መክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶቹ ግንባታ በመጓተቱ ምክንያት የጋምቤላ ስታዲዬምን ሳይጨምር በሰባቱ ፕሮጀክቶች ብቻ ከ264 ሚሊዮን ብር በላይ መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት በዘንድሮው በጀት አመት በተለይም የተጓተቱ ነባር ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በአጠቃላይ ለክልሉ ከተመደበው በጀት 30 ከመቶውን ለካፒታል በጀት በመመድብ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በ2015 በጀት ዓመት በተለይም የአምስቱ ቢሮዎች፣የልዩ ኃይል ካፕና የህዝብ መሰብሰቢያ አደራሽን ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው የተቋረጠውን የጋምቤላ ስታዲዮም ግንባታ ለማስጀመር እየተሰራ እንደሆነም አስታውቀዋል።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ቱት ኮር በበኩላቸው ከአራት ዓመት በላይ የተቋረጠውን የጋምቤላ ዘመናዊ ስታዲዮም ግንባታ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ እንደገና ለማስጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ተጀምሮ የነበረው የጋምቤላ ዘመናዊ ስታዲዬም ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ስራ 49 ከመቶ ደረጃ ላይ ደርሶ መቋረጡን አመልክተዋል።
የክልሉ የሴቶች የእግር ኳስ ፕሮጀክት አስልጣኝ ዬን ኒያል በሰጡት አስተያየት የጋምቤላ ስታዲዬም ግንባታ ሲጀመር የክልሉ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶት እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ግንባታው ከፍፃሜ ሳይደርስ በመቋረጡ የስፖርት ቤተሰቡ ቅር እንደተሰኘ ጠቁመው “መንግስት ህዝቡን በማስተባበር ጭምር የፕሮጀክቱን ግንባታ ለማስቀጠል መስራት አለበት” ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ በወቅቱ ባለመጠናቀቃቻው ህብረተሰቡ የሚጠብቀውን አገልግሎት ሊያገኝ አለመቻሉን የገለጹት ደግሞ የስፖርት ባለሙያ አቶ ሳሙኤል ታደሰ ናቸው።

በተለይም የጋምቤላ ስታዲዬም ባለመጠናቀቁ ወጣቱ ብሎም የአካባቢው ማህበረሰብ ከስታዲዬሙ የሚጠብቀውን አገልግሎትና ጥቅም ሊያገኝ አለመቻሉን ተናግረዋል።