በፕሮጀክቱ እየተተከሉ ያሉ ችግኞች የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ፋይዳቸው የጎላ ነው-ቢሮው

142

ጂንካ፤ነሐሴ 8/2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል በ30-40-30 የፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት እየተተከሉ ያሉ ችግኞች የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥና ኢኮኖሚውን የማሳደግ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን የክልሉ አርብቶ አደር ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው አመራሮችና ሰራተኞች “አሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ሀሳብ በኛንጋቱም ወረዳ አይፓ ቀበሌ በአንድ ጀምበር ከ5 ሺህ በላይ የፍራፍሬ ችግኞች ተከላና የበጎ አድራጎት ስራዎችን ዛሬ አካሂደዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የደቡብ ክልል አርብቶ አደር ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሎሬ ካኩታ በወቅቱ እንዳሉት ዝናብ አጠር በሆኑ ቆላማ አከባቢዎች በመስኖ የሚለሙ  ችግኞች ድርቅን ለመቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ።

በተለይም በክልሉ በ30-40-30 የፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት እየተተከሉና እየለሙ ያሉ ችግኞች እርጥበትን በመጠበቅ ድርቅን የመከላከል ስራን ከማገዝ ባለፈ የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና ኢኮኖሚውን ማሳደግ እንደሚያስችሉ ተናግረዋል ።

ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ድርቅ የመከላከል ስራን ዘላቂ ለማድረግና የምግብ ዋስትናን ችግር የመቅረፍ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ክልል በልዩ ትኩረት እየተካሄደ የሚገኘውን የ30-40-30 የፍራፍሬ ችግኝ ልማት ስራን በአርብቶ አደሩ አካባቢ በልዩ ትኩረት ማስፋት ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

አርብቶ አደሩን አካባቢው ላይ ባሉ ሰፋፊ ቦታዎች በኩታገጠም  በማደራጀት የድርቅ መከላከል ተግባሩን ዘላቂ ከማድረግ ባለፈ በዘርፉ የምግብና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማሳደግ እንደሚገባ አቶ ሎሬ አስገንዝበዋል ።

“በአካባቢው እንደ ኦሞ ያሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች፣ ለም አፈር እና ሰፊ የእርሻ ማሳዎች እያሉ ማህበረሰቡ ለዘመናት በድርቅና በረሃብ ሲጠቃ ነበር “ያሉት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ናቸው

የችግኝ ተከላ ስራን በማጠናከር በአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት አቀናጅቶ ማልማት ከተቻለ የኢኮኖሚ አቅማችንን ማሳደግና ድርቅን በዘላቂነት መቋቋም ይቻላል” ሲሉ አመልክተዋል  ።

አስተዳዳሪው አክለው “እየተተገበረ ያለው የ30-40-30 የፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክትን በማጠናከር የአርሶና የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትናና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል” ብለዋል ።

አካባቢው ላይ ያለውን ውሃ፤ ሰፋፊ መሬትና መሰል የተፈጥሮ ፀጋዎች ለፍራፍሬና ቅባት እህሎች ልማት አመቺ መሆኑን ጠቁመው  የግል ባለሀብቶች በአካባቢው በግብርና ልማት ላይ ተሳትፎ ቢያደርጉ ትርፋማ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።

ዛሬ ላይ የሚተከሉ ችግኞች በቂ እንክብካቤ ከተደረገላቸው አካባቢው በድርቅና በረሃ ሲጠቀስ የነበረውን ገፅታ በአጭር ጊዜ ሙሉ ሉሙ የመቀየር አቅም እንዳላቸው ገልጸው ለስኬታማነቱ አስፈላጊው ሁሉ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል ።

የደቡብ ክልል አርብቶ አደር ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች በኛንጋቶም ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ በበና ፀማይ ወረዳ ቀይ አፈር ከተማ ለአንዲት አቅመ ደካማ እናት የቤት እድሳት ስራ አስጀምረዋል።

በቢሮው አመራሮችና ሰራተኞች የገንዘብ ድጋፍ የተጀመረው የቤት እድሳት ስራው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተመላክቷል።

የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ የአመራሮቹና ሰራተኞቹ በችግኝ ተከላና በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ላደረጉት አስተዋጽኦ  አመስግነዋል።