በጉራጌ ዞን የቡኢ ከተማ፣ የደቡብ ሶዶ ወረዳ እና የሶዶ ወረዳ ምክር ቤቶች መንግስት ከአጎራባች የዞን መስተዳድሮች ጋር በአንድ የጋራ ክልል ለመደራጀት ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በመደገፍ የዞኑ ምክር ቤት ያሳለፈውን “በክላስተር አንደራጅም” ውሳኔ ውድቅ አደረጉ

343


ነሐሴ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጉራጌ ዞን የቡኢ ከተማ አማካሪ ምክር ቤት፣ የደቡብ ሶዶ ወረዳ ጊዜያዊ የአማካሪ ምክር ቤት እና የሶዶ ወረዳ ምክር ቤት መንግስት ከአጎራባች የዞን መስተዳድሮች ጋር በአንድ የጋራ ክልል ለመደራጀት ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በመደገፍ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ያሳለፈውን “በክላስተር አንደራጅም” ውሳኔን በሙሉ ድምጽ ውድቅ አደረጉ።
በትናንትናው ዕለት የቡታጅራ ከተማ፣ የመስቃን እና የምስራቅ መስቃን ወረዳዎች እና የማረቆ ብሔረሰብ ምክር ቤቶች እንዲሁም የቀቤና ብሄረሰብ ከአጎራባች የዞን መስተዳድሮች ጋር በክላስተር በአንድ የጋራ ክልል ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በመደገፍ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ያሳለፈውን “በክላስተር አንደራጅም” ውሳኔ ውድቅ አድርገዋል። በተመሳሳይ የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳም በተወካዮቹ በኩል የክላስተር አደረጃጀቱን መደገፉ ይታወሳል።
በዛሬው ዕለት ደግሞ በዞኑ ውስጥ የሚገኙት የቡኢ ከተማ አማካሪ ምክር ቤት፣ የደቡብ ሶዶ ወረዳ ጊዜያዊ የአማካሪ ምክር ቤት እንዲሁም የሶዶ ወረዳ ምክር ቤት መንግስት ከአጎራባች የዞን መስተዳድሮች ጋር በአንድ የጋራ ክልል ለመደራጀት ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በመደገፍ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ያሳለፈውን “በክላስተር አንደራጅም” ውሳኔን በሙሉ ድምጽ ውድቅ አድርገውታል።
ምክር ቤቶቹም የቀረበላቸውን መንግስትና ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ያቀረቡትን “በአንድ የጋራ ክልል መደራጀት” ምክረ ሃሳብ እና “የምስራቅ ጉራጌ የዞን ጥያቄ” አጀንዳን ተቀብለው በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል።
የቡኢ ከተማ አማካሪ ምክር ቤት በ5ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 2ኛ፥ የደቡብ ሶዶ ወረዳ ጊዜያዊ የአማካሪ ምክር ቤት በ4ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 2ኛ ዙር እና የሶዶ ወረዳ ደግሞ 4ኛ ዙር 10ኛ አመት ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤዎች የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ያሳለፈውን “በክላስተር አንደራጅም” የውሳኔ ሃሳብን ያለምንም ተቃውሞና ተዓቅቦ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ውድቅ አድርገውታል።
የቡኢ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የየወረዳዎቹ ዋና አስተዳዳሪዎች ከህዝብ የቀረበላቸውን ጥያቄ በዝርዝር ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበው በሙሉ ድምጽ አስጸድቀዋል።


የስራ ኃላፊዎቹ አክለውም ምክር ቤቶቹ ያሳለፉት የውሳኔ ሃሳብ ጥበብ የተሞላበት፣ አገር ያለችበትን ሁኔታ ያገናዘበ እና የህዝቦችን መስተጋብራዊ አንድነት ከግምት ያስገባ መሆኑን ተናግረዋል።
የየምክር ቤቱ አባላት የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ የተሳሳተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአጎራባች ወንድም ህዝቦች የመስተዳድር መዋቅር ጋር በአንድ የጋራ ክልል ለመደራጀት የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ የህዝቦችን፣ አብሮነት የሚያስቀጥልና ተቀባይነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የምስራቅ ቀጣና የጉራጌ ዞን አደረጃጀት እና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄም ቀጣይ በሚደራጀው የአንድ የጋራ ክልል አደረጃጀት ውስጥ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ያሳለፈውን የውሳኔ ሃሳብም አገር ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ የህዝቦችን የዘመናት አብሮነትና አብሮ የመልማት ፍላጎት ከግምት ያላስገባ መሆኑን አንስተዋል።
ከአጎራባች የዞን መስተዳድሮች ጋር በአንድ የጋራ ክልል ለመደራጀት መንግስት ያቀረበውን የውሳኔ ምክረ-ሀሳብ የአካባቢውን ማህበረሰብ የቀደመ አንድነት በማስቀጠል የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ በምክር ቤቱ ተንጸባርቋል።
በምክር ቤቶቹ ጉባኤም በምስራቅ ጉራጌ ከሚገኙ ብሔረሰቦች ጋር በአንድ ዞን መስተዳድር አደረጃጀት ምላሽ እንዲያገኝም ጠይቀዋል።
በምስራቅ ጉራጌ ዞን ለመደራጀት የቀረበው ጥያቄም ከህዝብ የሚቀርብን የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና የመልማት ጥያቄ መልስ ለመስጠት እንዲቻል መሆኑም ተገልጿል።