የቡልቡላ የተቀናጀ ኢንዱስትሪያል ፓርክን ስራ ለማስጀመር የሚያስችል የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እየተጠናቀቀ ነው

105

ነሐሴ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ)የቡልቡላ የተቀናጀ ኢንዱስትሪያልን ፓርክን ስራ ለማስጀመር የሚያስችል የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እየተጠናቀቀ መሆኑን የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የክልሉ መንግሥት የቡልቡላ የተቀናጀ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ያለበትን ሁኔታ የማስተዋወቅ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ማካሄዱን ተከትሎ 40 የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ፓርኩን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ባለሀብቶቹን ያስጎበኙት የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፕሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ልዩ አማካሪና የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሀሰን በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ለፓርኩ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን በሟሟላት ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚያስችል ተግባር ሲከናወን ቆይቷል።
በዚህ ረገድ የስድስት ሼዶች ግንባታ፣ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ፣የ50 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ እና የስድስት ውሃ ማከማቻ ታንከር ግንባታ ተጠናቋል ብለዋል።
እንዲሁም ለባለሀብቶችና አመራሮች አገልግሎት የሚሰጡ 68 የመኖሪያ ቪላ ህንጻዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለኪራይ ዝግጁ መደረጋቸውን አመልክተው፤የህፃናት ማቆያ ስፍራም መገንባቱን ጠቁመዋል።
ለፓርኩ የሚያስፈልገው 40 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሰብስቴሽን ዝርጋታ ውሰጥ 10 ሜጋ ዋት አገልግሎት መጀመሩን ጠቅሰዋል።
ዘመናዊ የገበያ ማዕከል፣የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ፣የስልጠና ማዕከል፣ፖሊ ክሊኒክ እና የፖሊስ ጣቢያ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሰዓት 12 ሺህ ሜትር ኩብ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማከማቻ ፕሮጀክት ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
ለፓርኩ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች ተሟልተው ለባለሀብቶች የማስተዋወቅ ስራ ውሰጥ መገባቱን ገልጸው፤በመንግስት ወጪ በ480 ሚሊዮን ብር ከተገነቡት ስድስት ሼዶች አምስቱ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መተላለፋቸውን አስታውቀዋል።
ፓርኩ ከ1 ሺህ 500 እስከ 20 ሺህ ካሬ ሜትር ሼዶችን የሚያሰራና መሠረተ ልማት የተሟላለት ተጨማሪ 150 ሄክታር መሬት እንዳለው ጠቅሰው፤ይህም ባለሀብቶችን እንደ የፍላጎታቸውና አቅማቸው ለማስተናገድ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የተዘጋጀው ሰፊ የሼድ መስሪያ ቦታ በጥራጥሬ፣በአትክለትና ፍራፍሬ፣ በማር፣በወተትና ወተት ተዋጽኦ ማቀነባበር፣በሥጋ እና በሌሎችም ምርቶች ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች መሰናዳቱን አስረድተዋል።
አሁን ላይ ባለሀብቶችን መጠባበቅ ብቻ ሳይሆን ያሉበት ድረስ በመሄድ በፓርኩ እንቅስቃሴ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት መጀመሩን ጠቁመዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኩን ከጎበኙ ባለሀብቶች መካከል ቢ ኤፍ ጂ የተሰኘ የታዳሽ ኃይል ካምፓኒ ባለቤት አቶ መላኩ ሃይሉ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ”ሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁሉም የልማት መስኮች ትልቅ እምርታ እያሳየችነው” ብለዋል።
በሀገሪቱ የሚገኙ የኢንዱስትሪያል ፓርኮች በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤በተለይ የቡልቡላ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የውጭ ባለሀብቶችን ጭምር የመሳብ አቅሙና ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
በጉብኝታቸው መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይ በ230 ሚሊዮን ብር ካፒታል በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮሰስ ውስጥ ያለውን ፍሳሽ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችል በታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት መስክ ለመሰራማት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ሌላኛው የጉብኝቱ ተሳታፊ እና የአሊቦስ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ተወካይ አቶ አብይ ግርማ በበኩላቸው የቡልቡላ ኢንዲስትሪ ፓርክ ደረጃውን የጠበቀና መሠረተ ልማት የተሟላለት ሳቢና ማራኪ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል።
በየትኛውም መስክ በፓርኩ የሚሳተፉ ባለሀብቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ድርጅታቸው ቡናና ጤፍ ማቀነባበርን ጨምሮ በሌሎችም መስኮች በመሳተፍ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸው፤ ለዚህም 100 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል እና ሁለት የሥራ መነሻ ሃሳብ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ክልሉ በቅርቡ የቡልቡላ የተቀናጀ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ያለበትን ሁኔታና አቅም ባስተዋወቀበት መድረክ ላይ መሳተፋቸውን የገለጹት ደግሞ የዮሴፍ ቢዝነስ ግሩፕ ተወካይ አቶ አያናው መርጊያ ናቸው።
ይሁን እንጅ ፓርኩ በዚህ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለው እንዳልገመቱና በአካል መጥተው ሲጎበኙ መደነቃቸውን ገልጸዋል።
በፓርኩ መሳተፍ እድለኝነትም ውጤታማም እንደሚያደርግ በጉብኝታቸው ወቅት ከተደረገላቸው ገለጻና ምልከታ ማረጋገጣቸውን ጠቅሰው፤በቀጣይ በፓርኩ የውስጥ ጥናት ላይ በተመሰረተ ስራ ላይ ለመሰማራት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የቡልቡላ የተቀናጀ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጅዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ይገኛል።