መዲናዋ የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ እቅድ ለማውጣት እየተዘጋጀች ነው

80
አዲስ አበባ መስከረም 7/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ እቅድ ለማውጣት ከአሜሪካ መንግሥት የዘርፉ ተቋም ጋር በትብብር ሊሰራ ነው። የአሜሪካ መንግሥት የአከባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በመዲናዋ ምክክር አካሄዷል። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰተው የአየር ብክለት ከተማዋ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል። በተለይም ደግሞ ከገጠር ወደ አዲስ አበባ በሚፈልሰው የሕዝብ ብዛትና የመዲናዋ ሕዝብ  ቁጥር ማሻቀብ ችግሩን በማስፋት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁንና የከተማዋ አስተዳዳርም መዲናዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን፣ መመሪያዎችንና መተዳደሪያ ደንቦችን አውጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። ያም ሆኖ የአየር ንብረትን በተመለከተ በቂ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የተቋማቱ ጠንካራ አለመሆንና በጉዳዩ ላይ  ተደጋጋሚ ጥናት አለመደረጉን እንደ ክፍተት ጠቅሰዋል። ከእነዚህ አሰራር ሥርዓቶች መካከል አንዱ የሆነውን የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ እቅድ ለመዘጋጀት ከአሜሪካ መንግሥት የአቅም ግንባታ ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል። የአየር ጥራት መቆጣጠሪያው እቅድ ተዘጋጅቶ ሲጠናቀቅም ለዘርፉ የፖሊሲ ቀራጪዎችና የውሳኔ ኃሳብ አቅራቢዎች መረጃ በመስጠት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ትሮይ ፊትሬል በበኩላቸው እቅዱን ለማዘጋጀት የአሜሪካ መንግሥት የአየር ንብረት ጥበቃ ኤጀንሲ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ያደርጋል። አሜሪካ ቀደም ሲል ከመዲናዋ ጋር በአየር ንብረት ጥበቃ ዙሪያ በጋራ ስትሰራ መቆየቷን አንስተው አጋርነቱ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም