የአረንጓዴ አሻራ ስኬት አገራችን ድንቅ መስራት እንደምትችል ትልቅ ማሳያ ነው -የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

179

ነሐሴ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአረንጓዴ አሻራ ስኬት አገራችን ድንቅ መስራት እንደምትችል ትልቅ ማሳያ ነዉ ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሃሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ/ም በይፋ ሲጀመር ለአራት ተከታታይ ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተጀመረ አገራዊ ፕሮጀክት ነበር፡፡
በዚህ መሰረት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላዉ ከተጀመረበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገራችን በቢሊየን የሚቆጠሩ የዛፍ ችግኞች ተተክሏል፡፡
ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ብቻ 18 ቢሊየን ችግኞች ተተክለዋል፡፡
በተያዘው የክረምት ወቅት ደግሞ ‟አሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ቃል 6 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ብቻ ከ6 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞች በላይ ማህበረሰቡን በማስተባበር ተተክለዋል፡፡
በያዝነው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የህብረተሰቡ ተሳትፎ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በዚህም 29 ነጥብ 46 ሚሊየን ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡
በአጠቃላይ እስከአሁን ድረስ ከ24 ቢሊዮን፣ 2 ሚሊዮን ችግኝ በላይ ተተክሏል፡፡
በዚህ የመጀመሪያዉ ዙር የመጨረሻ ዓመት ከተቀመጠዉ 20 ቢሊዮን አገራዊ ግብ በላይ ተጨማሪ 4 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል፡፡
ይህ በዐይነቱ የመጀመሪያ የሆነዉ ፕሮጀክት ከኢኮኖሚያዊና ስነምህዳራዊ ጠቀሜታዉም በላይ ያቀደነውን መጨረስ የምንችል፣ የመቻል አቅማችንን የሚያሳይ ታላቅ አገራዊ ድል ነዉ፡፡
ይህ ስኬት አገራችን በድርቅ ብቻ የምትታወስ አገር ሳትሆን ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ድንቅ ዉጤት ማስመዝገብ የምትችል መሆንዋን ለዓለም የሚያረጋግጥ ጨምር ነዉ፡፡
የፕሮጀክቱ ዓላማ የደን መመናመን አደጋን ለመግታት፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመቋቋም፣ የሚገነቡ ትላልቅ ግድቦችን ከደለል ለመታደግ፣ የተፋሰስና ደን ልማትን ለማረጋገጥ ነዉ።
በዚሁ መሰረት ላለፉት ሶስት የክረምት ወቅቶች በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብሮች ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እና ስነምህዳራዊ ጠቀሜታዎች ተገኝተዋል፡፡
ለአብነትም በ2013 ዓ.ም በተደረገ ጥናት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 17 ፐርሰንት ደርሷል፡፡
እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዛፎችን ከመትከል ባሻገር ለምግብነት የሚውሉ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞችን በማልማት በምግብ ዋስትና ራሳችንን የመቻል አቅማችንን ማሳደግ ተችሏል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብሩ ወንዞችን እና ምንጮችን በማጎልበት የበጋ የመስኖ ልማትን ማስፋፋት እና የተፋሰስ ልማት በየአካባቢው እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተጀምሯል፡፡
የአካባቢ መራቆትን እና የአፈር መሸርሸር መጠንንም በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ የሚያስችል ድንቅ ፕሮጀት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
በአነስተኛ መሬት ላይ ጥምር ግብርናን በማስፋፋት ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ለውጪ ገበያ የሚውሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን አምርቶ በመላክ የውጪ ምንዛሬ ማግኘት ተጀምሯል፡፡
የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ወንዞቻችን በደለል እንዳይሞሉም የአርንጓዴ አሻራ ልማቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡
በተጨማሪም በመላው ሀገሪቱ ባሉት 120 ሺሕ የችግኝ ጣቢያዎች አማካኝነት በርካታ የሥራ እድል ተፈጥሯል።
ከሁሉም በላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብሩ የማህበረሰቡ ዛፍ የመትከል ባህል እንዲጨምር አድርጓል፡፡
የተለያዩ መሪ ቃሎችን በመጠቀም ሰፊ የህዝብ ንቅናቄዎችም ተደርገዋል፡፡በዚህ መርሃ ግብር አማካኝነት ችግኝ በዘመቻ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማሳደግና ለውጤት ማብቃት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ግንዛቤ ማስፋት ተችሏል።
የአገር ኩራት የሆነዉ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት የተቀመጠዉን 20 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል ግብ መምታት ብቻም ሳይሆን ከአቀድነዉም አልፎ ከ24 ቢሊዮን በላይ ችግኝ እንድንተክል ብርድና ዝናብ ሳይበግራቸዉ የራሳቸዉን አሻራ ያኖሩትን ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች፡፡
በቀጣይ ለተተከሉ ችግኞች አስፈላጊዉን እንክብካቤ በማድረግ አገራዊ ግቦቻችን እንዲሳኩ ሁሉም የድርሻዉን እንዲወጣ መንግስት ጥሪዉን ያቀርባል፡፡