በአማራ ክልል በአሸባሪው የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት በተደረገው ጥረት ውጤታማ ስራ መከናወኑ ተገለጸ

78

ባህር ዳር ፤ ነሐሴ 7/2014(ኢዜአ) በአማራ ክልል አሸባሪው የህወሃት ቡድን ውድመት ያደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ በማደራጀት ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለማብቃት በተደረገው ጥረት ውጤታማ ስራ መከናወኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

የደረሰውን ጉዳት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተገንዝበው ድጋፍና ትብብራቸውን ማስቀጠል በሚቻልበት ላይ የተኮረ የምክክር ፎረም በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የቢሮ ሃላፊው ዶክተር መልካሙ አብቴ እንዳሉት፤  ባለፈው በጀት ዓመት አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ወረራ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

ከህልውና ጦርነቱ ጀምሮ ተጎጂዎችን አክሞ ለማዳን የሚያስችል የሰው ሃይል በመመደብ፣ የመድሃኒትና ቁሳቁስ በማቅረብ በኩል የገጠሙ ፈተናዎች ከባድ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ጦርነቱ እየገፋ ሲመጣም አሸባሪው ቡድን በደረሰበት አካባቢ ሁሉ የጤና ተቋማትን በማውደምና በመዝረፍ ህብረተሰቡ የህክምና አገልግሎት እንዳያገኝ እኩይ ድርጊት መፈጸሙን አመልክተዋል።

ከቡድኑ ሽንፈት ማግስት  ነጻ በወጡ አካባቢዎች የጤና ተቋማትን ፈጥኖ በማቋቋም፣ የሰው ሃይል በመመደብ፣ የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የእናቶች ወሊድና የህጻናት ህክምና ጨምሮ ለህዝቡ የመሰረታዊ ጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ መቻሉን ጠቁመው፤ ለተገኘው ውጤትም የአጋር ድርጅቶ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት ከዕለት ድጋፍ በመውጣት የወደሙ የጤና ተቋማትን በዘላቂነት ሚቋቋሙበት ዘመን በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

በቢሮው የእቅድ ግምገማ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር ዶክተር ሞገስ አስማረ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ወረራ በ1ሺህ 107 የጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመትና ዝርፊያ ከ13 ቢሊየን ብር በላይ እንደሆነ  በጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል።

ሆኖም  በክልሉ የበላይ አመራር የሚመራ ኮሚቴ በማዋቀርና ጉዳቱን የሚያጠና ቡድን በማቋቋም ፈጥኖ ወደ ስራ በመገባቱ የበርካታ ዜጎችን ህይወት መታደግ ተችሏል ብለዋል።

አሁን ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ባደረገው ርብርብ የጤና ተቋማቱን በወረራ ውስጥ ከነበሩበት ውድመት በመውጣት የተሻለ የመፈጸም አቅም እንዲኖራቸው ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በቢሮው የሃብት አሰባሰብ፣ አስተዳደርና አጋርነት ዳይሬክተር አቶ አዲስ አበባው ባቀረቡት ጽሁፍ፤  ተቋማቱ ፈጥነው እንዲደራጁ የክልሉ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ አጋር ድርጅቶች እያንዳንዱ ስድስት ሙያተኛ አባል የሆነበት 97 ተንቀሳቃሽ የህክምና ቡድን ፈጥነው በማሰማራት አርአያነት ያለው ተግባር መፈጸማቸውንም ጠቅሰዋል።  

የምክክር ፎረም ዓላማም ጉዳት የደረሰበት ህዝብ በሀገሪቱ ውስጥ የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ድጋፍና ትብብር የሚጠይቅበት ዓመት መሆኑን እንዲገነዘቡ ለማስቻል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም