የቱሪዝም ዘርፉን የማጠናከር፣ መዳረሻዎችን የማስፋትና የማስተዋወቅ ስራ ውጤታማ እየሆነ ነው- ቱሪዝም ሚኒስቴር

155

ነሃሴ 7/2014/ኢዜአ/የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ በሰው ሃይል የማጠናከር፣ መዳረሻዎችን የማስፋትና የማስተዋወቅ ስራ ውጤታማ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለ54ኛ ጊዜ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በእንግዳ አቀባበል፣ በምግብና መጠጥ ዝግጅት 296 ሰልጣኞችን አስመርቋል።

ኢንስቲትዩቱ በመደበኛ እና በተከታታይ የትምህርት ዘርፎች በሦስት በተለያዩ የክህሎት ሥልጠና ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በደረጃ ሁለት፣ በደረጃ ሦስት እና ደረጃ አራት አስመርቋል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ የቱሪዝም ዘርፉን በሰው ሃይል የማጠናከር፣ መዳረሻዎችን የማስፋትና የማስተዋወቅ ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

የቱሪዝም ዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በተለያየ የሙያ መስክ እየሰለጠነ ይገኛል ብለዋል።

ለዚህም ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመንግሥት በተጨማሪ የግሉ ሴክተር በዘርፉ በስፋት እንዲሳተፍ እንዲሁም የህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያድግ የተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሪፎርሙ ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት የልማት ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን ማደስና ማስተዋወቅ እንዲሁም አዳዲሶችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የሸገር ፓርኮችን ጨምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ፓርኮችን የማልማት ሥራ በስኬታማነቱ ቀጥሏል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገሪቱ ያሉትን የቱሪዝም መዳረሻዎችን በኦንላይን የማስተዋወቅና የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ የማራዘም ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዴኤታ ነቢያ መሐመድ፤ በቱሪዝም ዘርፍ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

May be an image of 1 person and standing

በቱሪስት መዳረሻዎች ዜጎች በተለያዩ ማህበራት በመደራጀት የሥራ እድል እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ከግል ባለሀብቶች ጋር በመሆንም በቱሪዝም ዘርፉ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው በቅንጅት እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ብቁ ሙያተኞችን በማሰልጠን ለቱሪዝም ዘርፉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ኢንስቲትዩቱ በቱሪዝም፣ በምግብ ዝግጅትና የእንግዳ አቀባበል የሰለጠኑ ተመራቂዎችን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ሰልጣኞች በበኩላቸው በተማሩት ትምህርት መስክ ባገኙት ዕውቀት አገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአገሪቱ እየተነቃቃ ባለው የቱሪዝም ዘርፍ በመግባት ለዕድገትና ዘመናዊ አሰራር የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ አረጋግጠዋል።