አምቡላንስን ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሲጠቀም የተገኘ አሽከርካሪ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ

87

መተማ ነሐሴ 7/2014 (ኢዜአ) የመንግስት አምቡላንስን ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሲጠቀም የተገኘ አሽከርካሪን በ8 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ አበበ ማሰሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የቋራ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የአምቡላንስ አሽከርካሪ የሆነ ግለሰብ  በህገወጥ መንገድ ሰዎችን በመጫን ወደ ጎረቤት ሀገር ለማሻገር በመሞከር  ወንጀል ተከሶ  ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ  የቅጣት ወሳኔ ተላልፎበታል ።

የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት የአምቡላንስ አሽከርካሪ ንጉሴ መኮንን የተባለ ግለሰብ  ከኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች የመጡን 21 ወጣቶች ከደላሎች በመቀበል ወደ ሱዳን ለማሻገር  በመሞከሩ ክስ የተመሰረተበት መሆኑን ተናግረዋል ።

ግለሰቡ  ወጣቶቹን በመጫን ግንቦት 21 ቀን 2014 ዓም  ከሌሊቱ 8:00 አካባቢ ገለጉ ከተማ አለሙ በር ተብሎ በሚጠራ ስፍራ  ሲደርስ በፀጥታ ኃይሎች እንዲቆም ቢጠየቅም ጥሶ ማምለጡን  ተናግረዋል ።

ተከሳሹ በጊዜው ቢያመልጥም የጫናቸውን ወጣቶች በጫካና በባዶ ቤት ውስጥ ደብቋቸው ባለበት ሁኔታ በፀጥታ አካላት ክትትል መያዙን አመልክተዋል።

ግለሰቡ የተሰጠውን ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተሳትፎ መገኘቱን ገልፀዋል።

ተከሳሹ የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ እያለ የመንግስትን አምቡላንስ ለወንጀል መፈፀሚያነት መጠቀሙና በአምቡላንሱ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

"ተከሳሽ ክሱን ክዶ ቢከራከርም ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ ጥፋተኝነቱ ተረጋግጧል"  ብለዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትላንት ባዋለው ችሎት የግለሰቡን ጥፋተኝነት በማረጋገጥ በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ውሳኔ ያሳለፈበት መሆኑን አመልክተዋል ።

"ፍርድ ቤቱ ግለሰቡ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/ 2012 አንቀፅ 8 (2-ሐ) መሰረት ተከሳሹን ያርማል መሰል የወንጀል ድርጊት የሚፈፅሙ ግለሰቦችን ያስተምራል በማለት በ8 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖበታል" ሲሉ የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ አበበ ማሰሬ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም