በዞኑ ለመጪው ትምህርት ዘመን ከ200 በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ነው

154

ነሐሴ 7/2014 ነቀምቴ /ኢዜአ/---በምሥራቅ ወለጋ ለመጪው የትምህርት ዘመን ከ200 በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በባለድርሻ አካላት ድጋፍ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቱሊ አዱኛ ለኢዜአ እንደገለጹት በሕብረተሰቡ፣ በባለ ሀብቶችና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፎ በዞኑ 17 ወረዳዎች 238 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ ያሉት ነው።

በዞኑ በመገንባት ላይ ካሉት ትምህርት ቤቶች መካከል እስካሁን 200 የሚበልጡት አብዛኛዎቹ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የቀሪዎቹም ግንባታ በመፋጠን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።  

ኅብረተሰቡን ጨምሮ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እየተገነቡ ያሉት  ትምህርት ቤቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ  እስከ 4ሺህ ሕፃናትን የማስተናገድ አቅም እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

በትምህርት ቤቶቹ ግንባታ እየተሳተፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ጥሬ ገንዘብን በማዋጣት፣ የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብና በጉልበት በመሳተፍ 1.1 ቢሊዮን ብር  የሚገመት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ተናግረዋል።

የሳሲጋ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሠረት ነጋሽ በበኩላቸው በወረዳው እየተገነቡ ካሉት 18 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መካከል እስካሁን የአራቱ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል።

ከትምህርት ቤቶቹ መካከል ስምንት የመማሪያ ክፍሎች ያሉት አንድ ሕንፃ ዴቨሎፕሜንታል ኤክስፐርትስ  ሴንተር በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ድጋፍ እየተገነባ ነው ብለዋል።

እንዲሁም ፉድ ፎር ሀንገር ኢትዮጵያ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ደግሞ አራት የመማሪያ ክፍሎች ያሉት አንድ ሕንፃ ገንብቶ ማጠናቀቁን አቶ መሠረት ተናግረዋል፡፡

የሌቃ ዱለቻ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ  አበራ ተስፋዬ በበኩላቸው በወረዳው 17 ትምህርት ቤቶች በህብረተሰቡ ተሳትፎ በመገንባት ላይ መሆናቸውን  አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም