ምክር ቤቶቹ ከአጎራባች የዞን መስተዳድሮች ጋር በክላስተር ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በመደገፍ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ያሳለፈውን "የክልል እንሆናለን" ውሳኔ ውድቅ አደረጉ

204

ነሐሴ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቡታጅራ ከተማ፣ የመስቃን እና የምስራቅ መስቃን ወረዳዎች እና የማረቆ ብሔረሰብ ምክር ቤቶች ከአጎራባች የዞን መስተዳድሮች ጋር በክላስተር በአንድ የጋራ ክልል ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በመደገፍ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ያሳለፈውን "የክልል እንሆናለን" ውሳኔ ውድቅ አደረጉ።

የዞኑን ምክር ቤት ውሳኔም አገር ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ የህዝቦችን የዘመናት አብሮነትና የልማት ተጠቃሚነትን የሚፃረር ሲሉ የየምክር ቤቶቹ አባላት ኮንነዋል።

የቡታጅራ ከተማ በ2014 ዓ.ም 4ኛ ዙር፣ የመስቃን ወረዳ በ2014 ዓ.ም 2ኛ ዙር፣ የምስራቅ መስቃን ወረዳ በ2014 ዓ.ም በ2ኛው ዙር፣ የማረቆ ብሔረሰብ ደግሞ በ2014 ዓ.ም 4ኛ ዙር አስቸኳይ የምክር ቤት ስብሰባቸውን ባደረጉበት ወቅት ነው የዞኑን ውሳኔ በሙሉ ድምጽ ውድቅ ያደረጉት።

May be an image of 2 people, people sitting, people standing and indoor

የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝቦች ክልልን ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት በሁለት ክልል በክላስተር ለማደራጀት የውሳኔ ሃሳብ መቅረቡ ይታወሳል።

የቀረበው ምክረ ሃሳብ ሁሉም የክልሉ ህዝብና መንግስት ኢትዮጵያ ያለባትን ጫና ከግምት በማስገባት ውሳኔውን ተቀብለው በየዞን ምክር ቤታቸው አጽድቀዋል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ግን ከአጎራባች የዞን መስተዳድሮች ጋር በክላስተር ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ምክረ ሃሳብ ውድቅ ማድረጉን መግለጹ ይታወሳል።

አጎራባች የዞን መስተዳድሮችን በክላስተር በክልል ለማደራጀት የቀረበው የውሳኔ ምክረ ሃሳብ ለኢትዮጵያና አካባቢው ማህረሰብ ወሳኝና ጠቃሚ ነው ያሉት የቡታጅራ ከተማ፣ የመስቃንና የምስራቅ መስቃን ወረዳዎች እንዲሁም የማረቆ ብሔረሰብ ምክር ቤቶች ከህዝብ ተወካዮች፣ ከየወረዳ አመራሮችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ምክክር በማካሄድ ከአጎራባች የዞን መስተዳድሮች ጋር በክላስተር ለመደራጀት በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

ምክር ቤቶቹ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ውሳኔ የህዝቦችን የጋራ አንድነት፣ አብሮ የመኖር ፍላጎትና መሬት ላይ ያለውን ሀቅ የሚፃረር መሆኑን በመጥቀስ ውሳኔውን ተቃውመውታል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ ላይ የሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ቅቡልነት እንዳለው ተደርጎ የተሰራጨው መረጃም ተቀባይነት የሌለውና መሰረተ ቢስ መሆኑ በምክር ቤቶቹ አባላት ተነስቷል።

መንግስት ያቀረበውን የውሳኔ ምክረ ሃሳብ በመደገፍም ከስልጤ፣ ከሀድያ፣ ከከንባታ፣ ሃላባና የም ህዝቦች ጋር በክላስተር በክልል ለመደራጀት መወሰናቸውን በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል።

መንግስት አጎራባች የዞን መስተዳድሮችን በአንድ የጋራ ክልል ለማደራጀት ያቀረበውን የውሳኔ ምክረ-ሃሳብ በመቀበል የምስራቅ ጉራጌ የዞን አደረጃጀት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ አጽንኦት በመስጠት በየምክር ቤቶቹ ውሳኔ ተላልፏል።

May be an image of 8 people and people standing

የማረቆ ብሔረሰብ ምክር ቤት አባላትም "የብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ወረዳ አደረጃጀት" ተፈቅዶ እራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳደሩበት ስርዓት እንዲፈጠርላቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

ከአጎራባች የዞን መስተዳድሮች ጋር በክላስተር በክልል ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ምክረ ሃሳብም ፍትሃዊ ተጠቃሚነትንና የዜጎችን አብሮነት የሚያስቀጥል እንደሆነ በምክር ቤት አባላት ተንጸባርቋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም