የህዝብ ሰቆቃ የማይገደው “በህዝብ ስም የሚነግድ ቡድን”

620

በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)

ሰላም እና ሰላማዊነት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለፍጡራን ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን የስነ መለኮት እና የስነ ልቦና ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡ ከሰላም እና ከሰላማዊነት የማያተርፍ ቢኖር እሱ ከሽብር ተግባራት የተጣባ ብቻ እንደሆነም ያስቀምጣሉ፡፡ የሽብር ተግብራትን የህልውና ጉዳያቸው የሚያደርጉ አካላት ሁሌም ከሰላም እና ሰላማዊነት በተቃራኒ መቆማቸው የተለመደ ነው፡፡ ይህ የባህሪ መገለጫቸውም ጭምር እንደሆነ ይገለጻል፡፡ እንደነዚህ አይነት ቡድኖች የራሳቸውን የሽብር ተግባራት ለመፈጸም እና ዓላማቸውን ለማሳካት ምሽግ የሚያደርጉት ስለሚተገብሩት ድብቅ የሽብር ተግባራትም ሆነ ፖለቲካዊ ዓላማ ምንም ግንዛቤ የሌለውን ንጹሁን ህዝብ እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡ 

የህዝብ የሰቆቃ ድምጾች

አሁን በኢትዮጵያ ሰሜኑ ክፍል የሚገኘው የህወሃት የሽብር ቡድን እያደረገ ያለውም ይህንኑ ነው፡፡ በሽብር ቡድኑ የመንቀሳቀሻ እና የመተንፈሻ አውድ ተነፍጓቸው ያሉ ህዝቦች ከነገ ዛሬ በፌዴራል መንግስቱ የቀረቡ የሰላም አማራጮች ተግባራዊ ተደርገው አሁን ካለንበት አስከፊ ህይወት እንወጣለን በሚል የሰላም አማራጩ ተግባራዊነትን በጉጉት እና በተስፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ዜጎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ “እዚህ ኑሮ ከብዶናል፤ እኛ ያለንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ህይወት እኛ ጋር ከባድ ነው፤ ትንሽ ጊዜው በመርዘሙም ችግሩን አከበደው፤ ህዝቡን በችጋር ሊጨርሱት ነው፤ ህወሃት የትግራይን ህዝብ መወከል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤ የህዝቡን ችግር ወደ ኋላ በማለት የሌብነት እና የዘረፋ ርብርብ ላይ ተጠምደዋል፤ ህዝቡን በማስያዣነት በመጠቀም ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት እየሰሩ ነው፤ በህዝብ ስም የሚመጣ ዕርዳታ ለወታደሮቻቸው ቀለብ ከማድረግ ባለፈ ራሳቸው በህገ-ወጥ መንገድ እየሸጡ ሀብት እያግበሰበሱበት ነው” የሚሉና መሰል የጭንቅ ድምጾች ከወደ ትግራይ ክልል መሰማት ከጀመሩ ሰንበትብት ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑን የፖለቲካ ቁማርተኝነት እና መንታ ምላስነት ባህሪ የተጠየፉ እና በጊዜ የነቁ ዜጎች ወደ አጎራባች ክልሎች በመሄድ ነፍሳቸውን ለማዳን ጥረት አድርገዋል እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ በሽብር ቡድኑ የመግደል፣ የማፈን፣ የማሰር፣ የማስፈራራት እና በባንዳነት እና በጠላትነት የመፈረጅ እኩይ ተግባር ምክንያት ወደ ጎረቤት ክልሎች ለመሸሽ ዕድሉን ያላገኙ ደግሞ ከቡድኑ የሚደርስባቸውን ስቃይ በመቻል በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፉ እንደሚገኙ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ለሰላም አማራጭ … የማያልቅ ትዕግስት

በአንድ ሀገር ውስጥም ሆነ በሌሎች ሀገራት ተፈልፍለው በሽብር ተግባራት ውስጥ የሚሳተፉ የሽብር ቡድኖች ፖለቲካዊ ዓላማቸው በውል የማይታወቅና ህልውናቸው የሚመሰረተውም በሽብር ተግባራት ላይ ብቻ ስለሚሆን መንግስታት ችግሩን በመፍታት የህዝባቸውን ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ ከጦር መሳሪያ በመለስ ያሉ የሰላም አማራጮችን ሁሉ መጠቀማቸው ከትክክለኛነትም በላይ የሆነ ውሳኔ መሆኑን በርካታ ማሳያዎችን በመጥቀስ የሚሞግቱ ምሁራን አሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በህወሃት የሽብር ቡድን እኩይ ተግባር ምክንያት ህዝቡ ከእስካሁኑ ጉዳት የባሰ ለከፋ ችግር እንዳይጋለጥ በማሰብ ከአንድም ሶስት እና አራት ጊዜ በላይ የተፈጠሩ ችግሮች የሀገርን ሉዓላዊነት እንዲሁም የህዝብን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ በሰላማዊ ውይይት ብቻ እንዲፈቱ የሰላም አማራጮችን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ወትሮውንም የህዝብን ችግር በመሳሪያነት መጠቀምን ዋና ተግባሩ ያደረገው የሽብር ቡድኑ ባይቀበለውም መንግስት በወሰደው የሰላም አማራጭ መንገድ ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ክልሉ መግባቱንና ህዝቡን ከከፋ ረሃብ አደጋ መታደግ መቻሉን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ መግለጹን ልብ ይሏል፡፡

ይሁንና የሽብር ቡድኑ አንድም ከጥፋት ያለመማር ሁለትም የሰላም አማራጭ ዕድሎችን በመልካም አጋጣሚነት በመጠቀም የህዝብን ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ ለፖለቲካዊ ነጥብ ማስቆጠሪያ እና የመደራደሪያ መሳሪያነት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡

በርካታ ሀገራት በድህረ-ግጭት ወቅት የድርድር እና ሰላማዊ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረጋቸው ካለተጨማሪ ውድመት እና ጉዳት ማምጣት የሚፈልጉትን ሰላም ማምጣት እንደቻሉ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ደጉ አስረስ እና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት መምህሩ ንጋቱ አበበ ከፋና ቴሌቭዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የበርካታ ሀገራት መንግስታት ከፍተኛ ጉዳት ካስከተሉ ጦርነቶች በኋላ ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር ያደረጓቸውን ሰላማዊ ውይይቶች እና ያስገኟቸውን ውጤቶች በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም አሁን በመንግስት የተጀመረው ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ የመስጠት ውሳኔ አዲስ ምዕራፍ ከፋች መሆኑን፤ መንግስት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያሳየ ያለው ሆደ ሰፊነት በአዎንታዊነት የሚነሳ እንደሆነ በመግለጽ ሌሎች ወገኖችም ልዩነታቸውን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ማምጣት አለባቸው ይላሉ፡፡

ህዝብን እንደግል ንብረት የመቁጠር ነባር አባዜ

ወትሮም ጭር ሲል አልወድም አይነት ባህሪ ያለው የሽብር ቡድኑ ከፌዴራል መንግስት የተዘረጉትን የሰላም አማራጮች በሙሉ ሲያመክን ቆይቷል፡፡ የሰላም አማራጭ የቡድኑ ህልውና ማብቂያ መሆኑን የሚረዳው ቡድኑ የህዝብ ሰቆቃ እንደማይጨንቀው በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የሽብር ቡድኑ የትግራይ ክልል እና ህዝብ የነፍስ አባት እኔ ብቻ ነኝ፤ ህዝቡ እኔ ከምከተለው የፖለቲካ መስመር ውጪ ሌሎች መስመሮችን መከተል አይችልም፤ ከኔ መስመር ውጪ የሚንቀሳቀሱ ሁሉ ጠላቶች ወይም የጠላት ተባባሪዎች አልያም ባንዳዎች ናቸው በሚል መፈረጅ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ለዚህም በቅርቡ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ለክልሉ ህዝብ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ እና መስመር አለን የሚሉ የፖለቲካ አደረጃጀቶችን የፈረጀበትና ያሸማቀቀበትን መግለጫ ማየቱ በቂ ነው፡፡ ቡድኑ በእርሱ የሽብር ተግባር ምክንያት ህዝቡ በችግር ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት ጭምር ይህን ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰቡ ላይ የሙጥኝ ማለቱን ላስተዋለ ቡድኑ ህዝብን ለፖለቲካ ትርፍ ማግኛ መሳሪያነት ከመጠቀም ባለፈ ለህዝብ ጥቅም መከበር እንዳልቆመ እና ወደፊትም እንደማይቆም መረዳት ይቻላል፡፡

ከዘህ ባለፈም በትግራይ ክልል የሚገኙም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ቡድኑ የክልሉን ህዝብ እንደማይወክል፤ በውስጡም በጥቅም የተሳሰሩ መሆናቸውን፤ ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ወደ ክልሉ እየገቡ ያሉ የሰብዓዊ ድጋፎችን ጭምር መቀራመት ላይ ማተኮራቸውን፤ ከቡድኑ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱትን ማፈን፣ ማሰር፣ መግደል እንዲሁም ማስፈራራት ላይ መጠመዱን የሚያመላክቱ መረጃዎች በስፋት እየወጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ዜጎች ይህ ቡድን ሀብትን በዘረፋ የማግበስበስ እና የስልጣን ጥሙን ለማሳካት ህዝብን ሲሳይ ማድረግ የቆየ ልምዱን አሁንም እየተጠቀመበት መሆኑን እየገለጹ ሰሆን ለዚህም፤ አሁን ላይ የትግራይ ህዝብ ሰቆቃ ይብቃ የሚሉ ድምጾችን ማፈን፣ አማራጭ ሃሳብ አለን እኛም የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ይመለከተናል እና መሰል ድምጾችን በማፈን በምትኩ የትግራይ ህዝብ ትግል አጨናጋፊዎች የሚል የዳቦ ስም በመስጠት ህዝቡን ወደ ከፋ የኑሮ ሰቆቃ ውስጥ እየከተተው መሆኑን በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡

የሽብር ቡድኑ የተለመደውን የሽብር ተግባሩን እንደሚቀጥል እየገለጸ ባለበት፣ ህዝብንም ለፖለቲካዊ ትርፍ ማግኛ መሳሪያ አድርጎ የመጠቀም አባዜውን ባልቀየረበት እንዲሁም የፌዴራል መንግስቱን በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ መድረክ የማሳጣት የየዕለት ተግባራት ላይ በተጠመደበት በዚህ ወቅት እንኳን የፌዴራል መንግስት ለህዝቡ ያለውን ወገንተኝነት ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲገባ በማድረግ እያሳየ ይገኛል፡፡ የፌዴራል መንግስት የያዘውን የሰላም አማራጭ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም የህዝብን ጥቅም በማይሸራርፍ መልኩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ በማንኛውም ጊዜ እና በየትኛውም ቦታ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለጸ ይገኛል፡፡ 

ከሰላማዊ አማራጩ በተቃራኒ የቆመ የዲፕሎማቶች ልዑክ እንቅስቃሴ

የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለሀገሪቱ የሚበጀው የሰላም ንግግር እንደሆነ በማወጅ የሚነጋገሩ አካላትንም ጭምር በመሰየም ለሰላማዊ አማራጩ ያለውን ቁርጠኝነት እያሳየ ይገኛል፡፡ ለዚህም ቡድኑ በፌዴራል መንግስት የተሰጠውን የሰላም አማራጭ ተጠቅሞ ወደ ውይይት እንዲመጣ ለማድረግ የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ አካላት መካከል ለሰላም አማራጩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ተብሎ የታመነባቸው የአሜሪካ፣ የአውሮፓና የአፍሪካ ልዩ መልዕክተኞችን እና የተወሰኑ ሀገራት አምባሳደሮችን ያካተተ ልዑክ ወደ ትግራይ ክልል ተጉዞ ከሽብር ቡድኑ ጋር ተወያይቶ መመለሱ ይታወሳል፡፡

የሽብር ቡድኑ በትክክልም የትግራይ ህዝብ ችግር እና መጎዳት የሚገደው ከሆነ የሰላም አማራጩን እንዲቀበል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ተብለው የተጠበቁት የአሜሪካ እና የአውሮፓ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች እንዲሁም በኢትዮጵያ የካናዳ እና የጣሊያን አምባሳደሮች ልዑክ የገደል ማሚቱ ይመስል በህዝብ ሞት እና እንግልት ፖለቲካዊ ጥማቴን አሳካበታልሁ በሚል ያስቀመጣቸውን ቅድመ-ሁኔታዎች መልሰው የማስተጋባት አዝማሚያ አሳይተዋል። ለዚህም ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰለማዊት ካሳ ልዩ መልዕክተኞቹ እና አምባሳደሮቹ ለሰላም ንግግር ጥረት ማድረግ ሲገባቸው በሌላ ወገን የተቀመጠ ቅድመ-ሁኔታ ላይ ተጠምደዋል እንዲሁም መንግስት ወደ ትግራይ የሚገቡ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቶች ባላቋረጠበት እና ክልከላዎች ባላደረገበት በዚህ ወቅት ቡድኑ የህወሃትን የውሸት ትርክት ማስተጋባቱ ስህተት ነው ሲሉ ወቀሳ የሰነዘሩት እና ያጣጣሉት፡፡

ልዩ መልዕክተኞቹ እና አምባሳደሮቹ መንግስት ለህዝቡ ጥቅም እና ለሰላማዊ አማራጭ ሲባል የወሰነውን የተናጠል ግጭት የማቆም ፖለቲካዊ ውሳኔን ተከትሎ ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፎች፤ የነዳጅ፣ የህክምና ቁሳቁሶች፣ የግብርና ግብዓቶች እና መሰል አቅርቦቶች ወደ ክልሉ እየገቡ መሆኑን እያወቁ ጭምር አይኔን ግምባር ያድርገው በሚመስል መልኩ፤ የጅል ለቅሶ ምልሶ መላልሶ እንዲሉ የሽብር ቡድኑ ፖለቲካዊ ጥሙን ለማሳካት እንደሽፋን የሚጠቀምባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ያደረገ መግለጫ ማውጣትን መርጠዋል፡፡

እነዚህ አካላት መንግስት ቀደም ብሎ ምላሽ የሰጠባቸውን ጉዳዮች ዳግም በማንሳት ወደ አንድ ወገን ያዘነበለ መግለጫ ሲያወጡ ሳት ብሏቸው እንኳን የሽብር ቡድኑ በክልሉ የሚገኙ ህዝቦች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ አድርግ፣ አማራጭ ሃሳብ ያላቸውን ሀይላት ከማሳደድ፣ ከመግደል፣ ከማሰር እና ከማፈን ታቀብ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው ወደ ክልሉ የገቡ በርካታ የጭነት ተሸከርካሪዎች ይመለሱ፣ የሽብር ቡድኑ እስካሁን በሀይል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የሚገኙ ህዝቦች ለከፋ ችግር ተዳርገዋል እና ከያዝካቸው አካባቢዎች ለቀህ ውጣ፣ ከፖለቲካዊ ጥቅም ይልቅ የህዝብን ጥቅም አስቀድም የሚል ነጥብ ለማካተት አለመድፈራቸው ትዝብት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ 

እንደመውጫ

የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ደጉ አስረስ እና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት መምህሩ ንጋቱ አበበ በጉዳዩ ላይ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ከግጭት የሚገኘው ውድመትና ጉዳት በመሆኑ ለሰላም አማራጮች ማመንታት አያስፈልግም፤ ለውጤታማነቱ የሁሉም ወገኖች በጎ ዕይታና ይሁንታ ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ፡፡ በመንግስት የተቀመጡት የሰላም አማራጮች ለሀገሪቱ ወርቃማ ዕድል፤ ለሽብር ቡድኖች ደግሞ ከሁሉ ጊዜ የታሪክ ተወቃሽነት እና ዘለዓለማዊ ጸጸት መውጪያ ብቸኛ መንገድ ነው የሚሉት ምሁራኑ ለሰላም የሚያስፈልገው ወጪ ሰላማዊ መንገድን ብቻ መከተል በመሆኑ ይህም ለጦርነት ከሚወጣው ከፍተኛ ወጪ አንጻር ሲታይ እጅግ ያነሰ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም የሚከፈልን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ሊሆን ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

የህወሃት የሽብር ቡድን በመንግስት የተቀመጠው ሰላማዊ አማራጭ እና ንግግር የህዝቡን ዘለቄታዊ ጥቅም እንደሚያረጋግጥ፤ በአንጻሩ ደግሞ ቡድኑ በህዝብ ስም እየነገደ ዕድሜን ለማራዘም የሚሄድበትን አውድ እንደሚሳጣው በውል በመገንዘቡ ሰላማዊ አማራጩ ተግባራዊ እንዳይሆን ለማድረግ የህዝቡን ጥቅም የማያስከብሩ ቅድመ-ሁኔተዎችን በመደርደር እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል፡፡ በችግር ውስጥ የሚገኘው ህዝብም ይህንን በስሙ እየነገደ ዕድሜውን ለማራዘም የሚሞክረውን ቡድን በቃህ፣ ከጫንቃዬ ላይ ውረድ ሊለው ይገባል፡፡ ሰላም ለፍጡራን ሁሉ!!!!!