ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል- የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

180

ነሐሴ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ መስክ ያስመዘገበችውን የበላይነት በቀጣይነትም ለማስቀጠል ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ።

በአስራ ዘጠነኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፎው አድርጎ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የዕውቅና መርሐግብር ተካሂዷል።

May be an image of 12 people and people standing

በመርሐግብሩ ላይ ንግገር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ የሚኒስቴሩ አንዱ ዓላማ ንቁ ዜጋና ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ነው ብለዋል።

ውጤት ያመጡት አትሌቶችም የነገ ተተኪዎች ናቸው ሲሉ ገልጸው በቀጣይም በሚደረጉ ዓለምሻምፒዮናዎችና የኦሊምፒክ ውድድሮች ተሳትፈው ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ አመልክተዋል።

የዛሬ ልፋታችሁ የነገ ድላችሁ ይሆናል ያሉት ሚኒስትሩ ለተመዘገበው ድል ዋንኛ ምክንያትም አትሌቲክሱን የሚመሩ ብቁ አመራሮች ስላሉና የስፖርቱ አካባቢ ሰላም በመሆኑና በተለይም በአትሌቲክሱ አካባቢ የነበረው ውዥንብር መጥራቱ እንደሆነ ገልፀዋል።

May be an image of 1 person, standing and indoor

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌድሬሽን ፕሬዘዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ድሉ የተገኘው በአገር ውስጥ የተለያዩ ውድድሮችና ሥልጠናዎች በመሰጠታቸው መሆኑን ተናግራለች።

የቡድን መሪዎች፣ አትሌቶችና አሰልጣኞች ቅንጅት የመጣ ውጤት መሆኑንም ነው የገለጸችው።

የድሉ ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብም እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም