የህዳሴው ግድብ ስኬት የህዝብና የመንግስት ቁርጠኛ አቋም ውጤት ነው-ነዋሪዎች

229

ዲላ/ሶዶ/አርባ ምንጭ፤ ነሐሴ 07/2014 (ኢዜአ)፡ የህዳሴው ግድብ ስኬት የህዝብና የመንግስት ቁርጠኛ አቋም ውጤትና የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭ ነው ሲሉ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌና የወናጎ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡


የአርባ ምንጭና ወላይታ ሶዶ ከተሞች ነዋሪዎች በበኩላቸው የታላቁ ህዳሴ  ግድብ 3ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸውን እና ግድቡ እስከሚጠናቀቅ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

 የይርጋጨፌና የወናጎ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በአንድ ቀን ልዩነት የግድቡ 2ኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመሩና ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙለት በስኬት መጠናቀቁ የተለየ ስሜትና ደስታ ፈጥሮላቸዋል።


ከይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪ መካከል አቶ አብዮት ኦዳ የህዳሴው ግድብ ስኬት የህዝቡና የመንግስት አንድነትና  ቁርጠኛ አቋም ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።


በተለይ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙለት በስኬት መጠናቀቁ ግድቡ ውጤታማ እንዳይሆን የተቀናጀ ጫና የሚያሳድሩ ሀገራትን ተስፋ የሚያስቆርጥ እና ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ደግሞ ተስፋችንን የምናድሰበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።


በግድቡ የታየውን ብሔራዊ አንድነትና መደማመጥ በሌሎች የልማት መስኮች በመድገም የሀገርን ዕድገት  በጽኑ መሰረት ላይ መትከል እንደሚገባ አመልክተዋል።


በተለይ ዕድገታችንንና ለውጣችንን የማይፈልጉ አካላት በሚሰጡን የጥፋት አጀንዳ ሳንወሰድ ድህነትን ማሸነፍ ላይ ብቻ ልናተኩር ይገባል ብለዋል።


ወይዘሮ ሰላማዊት በረከት በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ስኬት የህዝብና የመንግስት ቁርጠኛ አቋም ውጤት ከመሆኑ ባለፈ የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል።


 የሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው፤ካለፉት ጊዜያት በተሻለ ድጋፋቸውን በማጠናከር ግድቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።


የተሻለች ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ ማውረስ ካለብን በህዳሴው ግድብ ያሳየነውን አንድነትና ተነሳሽነት በሌሎች የልማት መስኮች ልንደግመው ይገባል ነው ያሉት።

 
የወናጎ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ራውዳ አብድቁ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ስኬት የአንድነታችንና የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭ ነው ብለዋል።


በአንድ ቀን ልዩነት 2ኛ ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመሩና ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙለት በስኬት መጠናቀቁ የተለየ ስሜትና ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።


በተለይ የተለያዩ ፈተናዎች በተጋረጡብን በዚህ ወቅት ይህን ብስራት መስማታችን የአንድነታችንና የጽናታችን ውጤት ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ለግድቡ ዘላቂነትና ለሌሎች ልማቶች ስኬት ወሳኝ ሚና ባለው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር  በመሳተፍና ለተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ በማድረግ የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ  የታላቁ ህዳሴ ግድብ 3ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸውእና የግድቡ ቀሪ ስራ እስኪሚጠናቀቅ ድረስ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች አስታውቀዋል።

የግድቡ ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት  አስተያየታቸውን  ለኢዜአ ከሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች መካከል  አቶ ነከረ ነጋሽ አንዱ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት በመንግስትና በዜጎች የተባበረ ክንድ ግንባታው በመፋጠን ላይ የሚገኘው የታላቁ  ህዳሴ ግድብ 3ኛው ዙር ውሃ ሙሌት ማጠናቀቁን ስሰማ ድርብ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።   

ግድቡ  የሀገርን የሃይል አቅርቦት ችግር ከመቅረፍ በላይ የኢንዱስትሪ አብዮቱን በማነቃቃት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ የሚያሳልጥ መሆኑን ተናግረዋል።

''የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ ለተሰለፉ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ዕድል ፋንታ ሳንሰጥ በየዓመቱ በድል ጎዳና ላይ መረማመድ የቻልነው መንግስትና ህዝብ እጅና ጓንት ሆነን መስራት በመቻላችን ነው'' ብለዋል።

 ለግድቡ ግንባታ በተደጋጋሚ ጊዜ ቦንድ በመግዛትና ስጦታ በማበርከት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያድርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ የግድቡ ቀሪ ስራ እስከሚጠናቀቅ ያልተቆጠበ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን  አረጋግጠዋል።

ሌላዋ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዘነበች መለሰ  በበኩላቸው ''የህዳሴው ግድብ  የኢትዮጵያ እናቶችን ከማገዶ እንጨት ሸክም የሚታደግ ተስፋችን በመሆኑ 3ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ እጅግ ደስ ብሎኛል'' ብለዋል።

በአንድነታችን ብዙ ፈተናዎችን እያሸነፍን እንደመጣነው ሁሉ በቀጣይም ግድቡን በአንድነት እንደጀመርነው  ለፍጻሜ እናበቃዋለን ሲሉ ገልጸዋል።

3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ቃልኪዳናችን እንድናድስ አነሳስቶናል ያለው ደግሞ ወጣት ደመቀ ደግፌ ነው።

''እኛ በሀገራችን ሉዓላዊነትና ልማት የማንደራደር ህዝቦች ነን'' ያለው ወጣቱ፤ የአሁኑ ትውልድ የሀገርን ሰላምና  ልማት በማረጋገጥ  እስከነ ክብሯ ለመጪው ትውልድ የማስረከብ ሃላፊነት እንዳለበት ተናግል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጪው ዘመን ለወጣቶች ብርሃን ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ገልጾ፤ ''የህዳሴ ግድብን በተባበረ ክንዳችን ለፍጻሜው በማድረስ  እንደ አይናችን ብሌን ልንጠብቀው ይገባል'' ብል።

 የህዳሴው ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን አንድሆነን ከተነሳን የሚያቅተን ነገር  አለመኖሩን ያረጋገጠ  በማለት የገለጹት ደግሞ  የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።

 አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በተለያየ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት አንድ ሆነን ስንነሳ የሚያቆመን የለም።

በብረታ ብረትና እንጨት ስራ የተሰማሩት አቶ ቸርነት ፋንታ እንዳሉት "የህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ በአንድነት ስንነሳ የማናሳካው ነገር አለመኖሩን ያረጋገጠ ነው" ብለዋል።

በተሰማሩበት የብረታ ብረት ስራ አልፎ አልፎ በሚከሰት የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ስራቸው ላይ መስተጓጐል እንደሚገጥማቸው የገለጹት ነዋሪው፤ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመሩና ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ በቀጣይ ችግሩ ይፈታል የሚል ተስፋቸውን እንዳለመለመላቸው ተናግረዋል።

የግድቡ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ እንዳስደሰታቸው ጠቁመው፤ በቀጣይም ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በሶዶ ከተማ በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ተስፋዬ ወልዴ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ገልጸው የተጀመረውን ግንባታ ከዳር ለማድረስ እንደሚተጉ ተናግረዋል።

"አንድነታችንን ካጠናከርን የማናሳካው የልማት ስራ እንደሌለ ከግድቡ ግንባታ አረጋግጫለሁ'' የሚሉት ነዋሪው ትብብሩን በማጠናከር በሌሎች የልማት ስራ ላይ መድገም እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የግድቡ ግንባታ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ የድርሻዬን ስወጣ ቆይቻለሁ ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አክሊሉ መና ናቸው።

ግድቡ ለስኬት በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ግድቡ ለፍጻሜ እስኪበቃ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም