የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት አይበገሬነታችንንና ዓባይን የብርሃን ምንጭ የማድረግ ውጥናችንን ያስመሰከረ ነው – አስተያየት ሰጪዎች

174

ነሐሴ 06 ቀን 2014(ኢዜአ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የኢትዮጵያውያንን አይበገሬነት ያሳየና ዓባይን የብርሃን ምንጭ የማድረግ ውጥናችንን ያስመሰከረ ነው ሲሉ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚኖሩ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በድል መጠናቀቁን በተመለከተ የባህርዳር ፣ መቱ ፣ሀረር ፣ጋምቤላ ፣ሰቆጣ፣ ሠመራ፣ ሚዛን አማን ፣ሻሸመኔ፣ ወላይታ ሶዶ፣ አዳማ፣ ደብረማርቆስና ወልድያ ከተሞች ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት “የታላቁ ሕዳሴ ግድባችን ሶስተኛ ዙር የዉሃ ሙሌት በሰላም መጠናቀቅ የኢትዮጵያን አይበገሬነት ማሳያ ነዉ።ኢትዮጵያ ለችግሮችና ለጫናዎች ሳትበገርና እጅ ሳትሰጥ የኖረች፣ ያለችና ያሰበችውን እያሳካች የምትቀጥል የአይበገሬነት ተምሳሌት ናት በማለትም ተናግረዋል።

“በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሌሎችም ጫናዎች ፕሮጀክቱን ማስቀጠልና ማሳካት መቻላችን የኢትዮጵያውያንን ቆራጥነትና ለችግሮች ያለመንበርከክ የአይበገሬነት ማሳያ ነው” ሲሉ ነው የገለጹት።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀከት ኢትዮጵያውያንን ከዐድዋ ቀጥሎ የአንድነት እና መተባበር ቃልኪዳናቸውን ለሁለተኛ ግዜ ያደሱበት ተግባር ነው በማለትም አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ልማታዊ እንቅስቃሴ በራሷ አቅምና ጉልበት መፈፀም እንደምትችል ለአለም ሁሉ በግልፅ ያሳየችበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የህዳሴው ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ከተነሳን የሚያቅተን ነገር አለመኖሩንም ያረጋገጠ ነው ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።

“አንድነታችንን ካጠናከርን የማናሳካው የልማት ስራ እንደሌለ ከግድቡ ግንባታ አረጋግጠናል፤ በሌሎችም የልማት ስራዎች ይሄን የአንድነትና የቁጭት ስሜት በመድገም ስኬታማ ልንሆን ይገባል” ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አገራችን ከድህነት እናቶቻችን ደግሞ እንጨት ከመሸከም የሚወጡበት ነው ሲሉም አስረድተው የኢትዮጵያዊያንን አንድነትና አሸናፊነት ዳግም ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

“የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 3ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ አባይን የብርሃን ምንጭ የማድረግ ውጥናችንን ከግብ እያደረስን ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው” በማለትም አመልክተዋል።

ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን እንደሚያደርጉ ገልጸው “በአንጡራ ሀብታችን የመጠቀም የዘመናት ቁጭታችንን በተግባር በማረጋገጥ ለመጪው ትውልድ ታሪክ መጻፍ የቻልንበት ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ” ተናግረዋል።