አረጋዊያን በሀገር ሰላም እሴት ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማጠናከር እየተሰራ ነው – ማህበሩ

123

አዳማ፤ ነሐሴ 06/2014(ኢዜአ) ፡- አረጋዊያን በሀገር ሰላም እሴት ግንባታና ግጭት አፈታት ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር አስታወቀ።

ማህበሩ ከአዳማና አካባቢዋ አረጋዊያን ጋር በሀገሪቱ  ዘላቂ ሰላም ቀጣይነትና አለመግባባቶችን በመፍታት በሚኖራቸው ሚና ዙሪያ ዛሬ በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ አካሄዷል።

የኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ክፍሉ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሀገሪቱን ሰላም ለማስፈን ግጭቶችና አለመግባባቶችን ለመፍታት የአረጋዊያን ሚና የጎላ ነው።

በዚህም የሀገራችን የሰላም ጉዳይ በቀዳሚነት የአረጋዊያን ጉዳይ መሆን አለበት ያሉት አቶ ጌታቸው፣  ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር  ለማላቀቅ የሚደረጉ ጥረቶችን በእውቀታችን  ለማገዝ ምን ማድረግ አለብን በሚለው ዙሪያ ለመምከር መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

አረጋዊያን የሀገር ባለውለታ፣ መሰረትና ምሰሶ ናቸው፤ በህዝቦች መካከል መቻቻል፣ አብሮነትና እሴትን ለማጠናክር የድርሻችንን መወጣት ስለሚገባን ነው ብለዋል አቶ ጌታቸው።

ፍላጎታችን በተለይ በየደረጃው ያሉ አረጋዊያን በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶችና አለመግባባቶችን በማስወገድ ሰላም ለማስፈን ከኛ ምን ይጠበቃል የሚለውን የጋራ ግንዛቤ ይዘን የድርሻችንን ለመወጣት ነው ብለዋል።

የሀገሪቱ ህዝቦች የሚፈልጉት  ሰላምና ልማት በመሆኑ የበኩላቸውን ለመወጣት  እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

አረጋዊያን ሀገርን በማረጋጋትና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ሰላምን በማስፋን ሂደት ሚናቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ  የቦርዱ ፀሓፊ መቶ አለቃ በቀለች ሞሲሳ ናቸው።

በተለይ ወጣት ጥፋተኞችን በመገሰፅና በመምከር የአካባቢያቸውንና ሀገርን ሰላም በማስፈን ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ይሄንን ሚናቸውን ይበልጥ ለማጠናከር  ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።

በግጭቶች በዋናነት የሚጎዱት አረጋዊያንና ሴቶች ናቸው ያሉት መቶ አለቃ በቀለች፤ በተለይ አረጋዊያን በሽምግልና፣ በእርቅና ባህላዊ የግጭት አፈታት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በማህበራዊ ትስስር፣ የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ረገድ የነበራቸውን ሚና አሁን ይበልጥ እንዲያጎለብቱ በአቅም ግንባታ ለመደገፍ ጭምር እየሰራን ነው ብለዋል።

የአዳማ ከተማ አረጋዊያን ማህበር ሊቀመንበር አቶ አክሊሉ ያደቴ በበኩላቸው ፤ አረጋዊያን ሀገራችን አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሰላም ጉዳይ የሁላችንም መሆኑን ተገንዝበን በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።

በተለይ ከጥቅማቸው አኳያ የሀገራችንን ሰላም የሚያደፈርሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሴራ በትብብር ለማክሸፍ  የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

ባህላዊ ስነ ምግባር ማዳበር፣ ግብረ ገብነት በየደረጃው ባሉ የትምህርት ተቋማት እንዲጎለብቱ ፣ የስነ ዜጋ ትምህርት እንዲስፋፋና የአብሮነት እሴት እንዲዳብር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።