ኢትዮጵያውያን በወንድማማችነት መንፈስ ከተባበርን ችግሮችን በቀላሉ መፍታት እንችላለን - ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኤለማ አቡበከር

95

ነሃሴ 06 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን የሚገጥሙንን ፈተናዎች በወንድማማችነት መንፈስ ለመፍታት እየተረዳዳንና እየተጋገዝን ከሄድን ወደ ስኬት በቀላሉ መድረስ እንችላለን ሲሉ የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኤለማ አቡበከር ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በክልሉ በጭፍራ ወረዳ በጦርነት የወደሙ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር የመሰረተ ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት ነው፡፡

በወቅቱ ባደረጉት ንግግር "አሸባሪው ህወሃት በሀገር ላይ የደቀነዉን አደጋ በመቀልበስ ሁሉም ኢትዮጵያዉያን በጋራ ተረባርበዉ አክሸፈዋል" ነው ያሉት።

ይሁንና በክልሉ ከ21 በላይ በሆኑ ወረዳዎች ጦርነቱ ትቶ ያለፈዉ ሰብአዊ፣ ሰነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመት በቀላሉ የሚገመት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን የሀገራቸዉን ህልውና ለማረጋገጥ ያሳዩት ወንድማዊ ትብብርና አጋርነት በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ መገንባት ላይ በመድገም በሀገራዊ ብልጽግና ማሳካት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴርና አጋሮቹ በክልሉ የወደሙ ትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት የዚሁ ወንድማዊ አጋርነት መገለጫ ነው ብለዋል።

ይህን ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸዉ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርእሰ-መስተዳድሩ ይህ የትብብር መንፈስ በሁሉም የልማት መስክ መድገም እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፊሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸዉ የሽብር ቡድኑ በአማራና አፋር ክልል በወረራ በያዛቸውአካባቢዎች ከ1ሺህ 200 የትምህርት ተቋማትን ማውደሙን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴሩ በጦርነቱ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን በተሻለ ይዘት ገንብቶ ወደስራ ለማስገባት የተለያዩ ባለድርሻ አካሎችን አስተባብሮ አየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የዛሬው የጭፍራ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ በ60ሺ ካሬሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን አጠቃላይ የገንዘብ ወጪዉ ሜንሺን ፎር ሜንሺን በተባለ ግብረሰናይ ድርጅት የገንዘብ ወጪ የሚሸፈን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስራዉም ከ9ወራት ባነሰ ግዜ ተጠናቆ ወደአገልግሎቶት የሚገባ ሲሆንበቀጣይ በተመሳሳይ በጦርነቱ የወደሙ የትምህርት ተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል፡፡

የሜኔሺን ፎር ሜንሺን ፋዉንዴሺን የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ይልማ ታየ የትምህርት ቤቱ ግንባታ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣዉ ስታንዳርድ መሠረት የሚገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የሚያስፈልገውን 23 ሚሊዮን ብር የሚሸፍን መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም