አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ያስተማራቸው የውጭ ሃገራት ዜጎችን ጨምሮ ነገ 1 ሺህ 132 ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ አስታወቀ

አሶሳ ፤ ነሐሴ 06 / 2014 (ኢዜአ) አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ያስተማራቸውን የውጭ ሃገራት ዜጎችን ጨምሮ ነገ 1 ሺህ 132 ተማሪዎችን ለማስመረቅ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ለዘጠነኛ ጊዜ ነገ የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች በመደበኛ፣ በማታ እና በክረምት መርሃ ግብር በድህረ ምረቃ እና ቅድመ ምረቃ ፕሮግራም ትምህርታቸውን የተከታሉ ናቸው።

ከተመራቂዎች መካከል የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሌ ላንድ እና ሌሎችም የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች የሆኑ ስደተኞች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው መማር ማስተማሩን ለማቀላጠፍ ሰሞኑን ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

የማስፋፊያ ግንባታው የድህረ ምረቃ ማዕከል፣ የተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ፣ የግብርና እና ተፈጥሮ ሃብትን ፣የኢንፎርማቲክስ እና ቴክኖሎጂን ህንጻዎችን እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡

የማስፋፊያው ግንባታ በየዓመቱ ተጨማሪ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል እንደሚያስችል  ዶክተር ከማል ተናግረዋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ  በአሁኑ ወቅት ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም