የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመንግስትንና የህዝብን የልማት ትብብር ያረጋገጠ ነው-- ነዋሪዎች

189

መተማና፤ ደብረ ማርቆስ ነሐሴ 6/2014 (ኢዜአ)፡ ''የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጭት መጀመሩ የመንግስትና የህዝብን የልማት ትብብርና በፈተና ውስጥ ስኬት ማምጣት እንደሚቻል በተጨባጭ ያሳየ መሆኑን የገንዳ ውሃና ደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

270 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው  ሁለተኛው ተርባይን  ትናንት  ሃይል ማመንጨት ጀምሯል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አባተ ነጋ ለኢዜአ እንዳሉት በህዝባዊ አንድነትና ትብብር የተጀመረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በችግሮች ውስጥ አልፎ ሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመሩ በየትኛውም ፈተና ውስጥ ቢሆን በፅናት ከተሰራ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያስምሰከረ ነው።

''ይህ ስኬት የኢትዮጵያን ከፍታ ለሚመኙ የደስታ ምንጭ ውድቀቷን ለሚመኙ ደግሞ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው'' ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የወር ደሞዛቸውን ለ2 ጊዜ ማበርከታቸውንና የ5 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ህዝቡ ለህዳሴው ግድብ ከሚያደርገው የገንዘብ ደጋፍ በተጨማሪ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅም ለሌላ ተጨማሪ ድልና ብስራት መስራት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ቄስ ረዳ ላቀው በበኩላቸው አሻራቸው ያረፈበት የህዳሴ ግድብ ለፍሬ መብቃቱ  የሀገሪቱ ቀጣይ ጉዞ በብርሃን የታጀበ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

''ከዚህ ቀደም ለአራት ጊዜ ያክል በቦንድ በመግዛት የድርሻዬን ተወጥቻለሁ'' ያሉት ነዋሪው፤ በቀጣይም የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ግድቡ የአዲሱ ትውልድ ደማቅ አሻራ መሆኑን ያመለከቱት ነዋሪው፤  ''የግድቡ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያ በጠንካራ ልጆቿ የተባበረ ክንድ ፈተናን ወደ መልካም እድል መቀየሯን ያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል።

''አትገነቡም ሲሉን ገንብተን፣  በሁሉም ነገር አትችሉም ሲሉን በሁሉም ነገር ችለን ተጨባጭ የመቻል እውነትን እኛ ኢትዮጵያውያን ለአለም ሁሉ ከፍ አድርገን አሳይተናል'' ብለዋል።

''የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ሀይል ማመንጨት መጀመሩ የአላማን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ  ነው'' ያሉት ደግሞ የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ አይንሸት ባህታ ናቸው።

የኢትዮጵያዊያን የአላማ ጽናት እና የተጠናከረ አንድነት ስንጓጓለት የነበረው የህዳሴ ግድብ 2ኛ ተርባይን ሃይል ማመንጨት እንዲጀምር ማስቻሉን አመልክተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ተንሳኤ ለማብሰር እና ከድህንት ታሪክ ለመውጣት  አብሮነታችንና አንድነታችንን   በማጠናከር እንቀጥላለን ብለዋል።

አቶ ሚካኤል ማርቆስ በበኩላቸው የኮንስትራክሽን ሰራተኛ ሆነው በህዳሴ ግድቡም ይሰሩ እንደነበር ገልጸው፤ የውስጥ አንድነት ካለ የማያልፍ እና የማይደረስበት ለውጥ እንደሌለ ማሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራችን ያለችበት እና ያሳለፈችው ተደራራቢ ችግሮች የበረቱባት ቢሆንም የግንባታው አላማ ኢትዮጵያን ማሻገር በመሆኑ የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛው ተርባይን ሃይል ማመንጨት እውን ሆኗል ብለዋል።

ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ተስፋን በመሰነቅ ካለቸው እየቀነሱ ያደረጉት አስትዋጽኦ ፍሬ በማሳየቱ መደሰታቸውነ  የገለጹት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ አብርሃም ቀለሙ ናቸው።

የህዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ሀገራት ሁሉ እድገት እና ኩራትን የሚያጎናጽፍ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛው ዞር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሥፍራው ተበስል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት አባይ የኢትዮጵያ  ብቻ ሳይሆን ለአለም የተሰጠ ስጦታ ነው።

ሶስተኛው ዞር የውሃ ሙሌት ክንውን አምና ከነበረው ጋር ሲነጻጸር 575 የነበረው ከፍታ ዘንድሮ በ25 ሜትር ጨምሮ 600 ሜትር ከፍታ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም