ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግና የጀመረችውን ጉዞ ትቀጥላለች- አቶ ኦርዲን በድሪ

138

ሐረር፤ ነሐሴ 6/2014 (ኢዜአ)፡ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግና የጀመረችውን ጉዞ ትቀጥላለች ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በድል መጠናቀቁን በማስመልከት ዛሬ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ”ሀገራችን ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግና የጀመረችውን ጉዞ ትቀጥላለች” ብለዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ”የኢትዮጵያዊነታችን አርማ የጋራ ጥረታችን አሻራ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ላመነጨበት ለዚህ ታሪካዊ ቀን እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል።

አቶ ኦርዲን በድሪ ኢትዮጵያዊያን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለስኬት እንዲበቃ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበትና በሀሳብ አሻራቸውን ማኖራቸውን ገልጸው፤ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ”የልፋታችሁን ዋጋ እንኳን ለማየት አበቃችሁ” ብለዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያም ፈተናዎችን በብቃት እያለፈች ወደ ብልጽግናዋ መገስገሷን ትቀጥላለች ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ለክልሉ ህዝብና ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።