የዳያስፖራው ማሕበረሰብ የውጭ ጫናንና ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ረገድ አሁንም ጠንካራ እንቅስቃሴ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ

142

ነሐሴ 6 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማሕበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣ የውጭ ጫናንና ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ረገድ አሁንም ጠንካራ እንቅስቃሴ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የተለያዩ ዲያስፖራዎች ተናገሩ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ሲቃጣ የቆየውን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ጫናን ለመከላከል ዳያስፖራዎች በያሉበት ሀገር ያለምንም ልዩነት በጋራ በመቆም ሲታገሉ ቆይተዋል።

ዳያስፖራው ማሕበረሰብ በተለይ በ#NO MORE ወይም ˝በቃ˝ ንቅናቄ አማካኝነት የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ያሳዩት ሀገር ወዳድነት መቼም የሚዘነጋ አይደለም።

በዳያስፖራው ወቅታዊ ሀገራዊ ተሳትፎ ዙሪያ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በውጭ የሚኖሩ ዜጎች የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማስተባበር በኢትዮጵያ የልማትና የኢንቨስትመንት ጉዞ በንቃት መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ የሆኑት የ'ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን' የሚዲያ ክፍል ሀላፊ አቶ አንዋር መሀመድ ዳያስፖራው የውጭ ጫናንና ጣልቃ ገብነትን በመከላከል ረገድ አዎንታዊ ሚና እንደነበረው አንስተዋል።

ዳያስፖራው በዚህ ረገድ የተጫወተውን ገንቢ ሚና በሀገር ልማት ላይ በመድገም በአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት የራሱን አሻራ ማሳረፍ አለበት ብለዋል።

ዳያስፖራው በቆይታው ያካበተውን እውቀቱንና ሃብቱን በማፍሰስ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ወደፊት ለማራመድ ለተነደፈው የኢትዮጵያ ብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

May be an image of 1 person

ከቨርጂኒያ የመጡት የ'በድር ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል' ፕሬዚዳንት አህመድ ወርቁ በበኩላቸው ዳያስፖራው በተደራጀ መንገድ በኢትዮጵያ ላይ ተከፍቶ የሰነበተውን የውጭ ጫናንና ጣልቃ ገብነትን በመከላከል ረገድ የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ የውጭ ጫናዎችን በዘላቂነት ለመቋቋም የውስጥ የልማት አቅምን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ ዳያስፖራው በሀገር ልማት ላይ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት ብለዋል።

May be an image of 1 person

ነዋሪነታቸው ስዊዘርላንድ ጄኔቭ የሆነው አቶ ቅጣው ያየህራድ በበኩላቸው ዲያስፖራው የተለያዩ ፍላጎቶች ቢኖሩትም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አንድ በመሆን የውጭ ጫናንና ጣልቃ ገብነትን በፅናት መከላከሉን በበጎ አንስተዋል።

ይህንኑ አወንታዊ ተሳትፎ በልማቱ ላይ በመድገም በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ የራሳቸውን አሻራ ሊያሳርፉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም