ኅብረሰተቡ ስለ ሀገራዊ ምክክሩ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ የምክክር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን እንሰራለን-የምክር ቤት አባላት

92

ሚዛን አማን፣ ነሀሴ 06/2014 (ኢዜአ) ለኅብረሰተቡ ስለ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ በቂ ግንዛቤ በመስጠት ለስኬታማነቱ እንደሚሰሩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አባላት አስታወቁ።

የምክር ቤቱ አባል አቶ መስፍን መንገሻ ለኢዜአ እንዳሉት ችግሮችን መፍታት የሚቻለው ከአንዱ ወደ አንዱ በመወርወር ሳይሆን በጋራ በመነጋገርና  በመስማማት ነው።

"የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ እንደ ሀገር አስፈላጊነቱ ታምኖበት የተቋቋመውን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የመደገፍ ሀገራዊ ግዴታችንን እንወጣለን" ብለዋል።

"ለብሔራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም መስፈን ተስፋ የተጣለበት የሀገራዊ ምክክር ሂደት የታለመውን ግብ እንዲመታ የሚጠበቅብኝን ሁሉ አበርክቶ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ" ስሉም አረጋግጠዋል።

ብሔራዊ የምክክር ሂደቱን ለማሳለጥ ሃላፊነት የተጣለበት ኮሚሽኑም ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ ከፈተናዎች የሚያሻግር ትልቅ ኃላፊነት ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ መስፍን "ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በድል ስትሻገር እኛም ወደ ከፍታ እንሻገራለን" ሲሉ ገልጸዋል።

በአካባቢያቸው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ የምክክር ሥራው ስኬታማ እንዲሆን ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

አሁን ኢትዮጵያ እየገጠማት ካለው ችግር አንጻር ዘላቂ ሀገራዊ የሰላም መፍትሄ ለማምጣት ኮሚሽኑ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ጠቅሰው በማንኛውም ሁኔታ ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ዳዊት ተሰማ በበኩላቸው "የብሔራዊ ምክክር ሂደቱ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት መሠረት መጣል የሚችል እንዲሆን በጋራ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

በምክክር ሂደቱ በህዝብ ውስጥ የቆዩ አላስፈላጊ ሰንኮፎች ተነቅለው ፍቅርና አንድነት እንዲሰርጽ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ዳዊት ገልጸዋል።

"ሀገራዊ ኮሚሽኑ ባህላዊ የኢትዮጵያ የሰላም እሴቶችን በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለው ዝግጅት የሚበረታታና ተስፋችንን ከፍ የሚያደርግ ነው" ያሉት ደግሞ  ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ክፍሌ ኃይለጊዮርጊስ ናቸው።

በአካባቢያቸው ያለውን የህብረተሰብ የአኗኗር ዘዬና እሴት በማሳወቅ ረገድ የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እንደ ህዝብ ተወካይ ለማስተባበር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"መደማመጥና ችግሮችን በእርቅና ይቅርታ መፍታት ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም " ብለዋል።

ሰላምን በማስቀደም በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት የማይፈታ ችግር እንደሌለ ገልጸው "ምክክርን የነገሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ አድርገን መጠቀም አለብን" ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም