የህዝቦችን ሰላምና አንድነት ማጎልበት የዕለት ተዕለት ተግባራችን ሊሆን ይገባል- የሃይማኖት አባቶች

95

ሐረር፤ ነሐሴ 6/2014(ኢዜአ) የህዝቦችን ሰላምና አንድነት ማጎልበት የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት ተግባር ሊሆን እንደሚገባ በሐረሪ ከልል የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

የሃይማኖት አባቶቹ ለኢዜአ እንዳሉት፤  የኢትዮዽያን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል።

 ከክልሉ የሀይማኖት አባቶች መካከል መጋቢ ሃዲስ ቆሞስ አባዝራ ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት፤ “በሁሉም የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት የሚሰጡ ትምህርቶች ኢትዮዽያዊነትን የሚያጎለብቱ፣ ሰላምና አንድነትን የሚያመጡ  መሆን አለባቸው ብለዋል።

ይህም በህብረተሰቡ መካከል አንድነትና ሰላምን ለማምጣት የሚከናወነው ስራ ቀላል ያደርገዋል ያሉት መጋቢ ሃዲስ ቆሞስ አባዝራ፤ በተለይ ህብረተሰቡ በማህበራዊ የትስስር ገጽ እና በሌሎች የሚያስተላልፋቸውን ሃሳቦች መመርመርና ማጤን እንደሚገባው  ተናግረዋል።

ሰው ሰርቶ የሚገባው፣ ሃይማኖታዊ ስርዓትም የሚተገበረው ሰላም ሲኖር ነው ያሉት ደግሞ  ሼክ ታጁዲን አህመድ ናቸው።

ከሁሉም በፊት ሰላም አስፈላጊና ለዚህም ተግቶ መስራት፤ በተለይ በህብረተሰቡ መካከል ሰላምና አንድነትን በማጎልበት አንድ ሆነን ሀገርን ማልማት ይጠበቅብናል ነው ያሉት ሼክ ታጁዲን።

በብሔርና  ሃይማኖት ባለመለያየት አንድ በመሆን በልማት ላይ መረባረብ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም  ሁሉም የሰላምና የአብሮነት ስራን የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት ተግባር ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ፓስተር ዮሴፍ ሃብተማርያም  በበኩላቸው፤  ሰላም በማጣት የሚጠቀሙት የተወሰኑ አካላትን ተግባር ሁሉም ከመንግስት ጎን ተሰልፎ የመታገል ሃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ፓስተር ዮሴፍ ፤  የኢትዮዽያን ሰላም የማይፈልጉ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ሀገራችንን ለማፍረስና ህብረተሰቡን ለመከፋፈል ቀን ሌሊት እየጣሩ ስለሚገኙ  ህብረተሰቡ አንድነቱን ማጠናከር ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።

 እድሮች፣የወጣት ማህበራት፣የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎችም ስለ ሰላምና አንድነት የማስተማር ስራን የዕለት ተዕለት ተግባር ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።