የታችኛው ተፋሰስ አገራት ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የአካባቢ ልማትና ጥበቃ ሥራ የሥነ-ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ሊፈጽሙ ይገባል

89

ነሀሴ 6/2014 /ኢዜአ/ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የአካባቢ ልማትና ጥበቃ ሥራ የሥነ-ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ሊፈጽሙ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ።

ግብጽ ከወራት በኋላ በምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎቿን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተግባቦት ሥራ ለመሥራት ከወዲሁ ልትዘጋጅ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስን ጨምሮ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ገባሮቻቸው ዘላቂ የውሃ ፍሰት እንዲኖራቸው በአፈር፣ ውሃና ስነ-ህይወታዊ ዘዴዎች የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ማከናወን ከጀመረች ውላ አድራለች።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሞቱማ ቶሌራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የምታከናውነው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለዓባይ ወንዝ ሕልውና መሰረት ነው።

በዚህም የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ለሥርዓተ-ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ሊከፍሉ ይገባል ባይ ናቸው።

የዓባይ ወንዝን ለንትርክ ሳይሆን ኢትዮጵያ የምታከናውነውን የተፋሰስ ልማት በመደገፍ ለጋራ ተጠቃሚነት መተባበር ይገባል ነው ያሉት። 

የደን ተመራማሪውና ብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ እንዲሁ፤ በውሃ ለተሳሰሩት የአፍሪካ ቀንድ አገራት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ለአገራቱ ውሃ ታፈሳለች ይላሉ።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ የምታከናውነው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ችግኝ ተከላ አቅም ኖሯት ሳይሆን ለአገራት የጋራ ጥቅም ለሆነው ለአካባቢያዊ ስነ-ምህዳር ጥበቃ በማሰብ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብም ለሚያደርገው ውለታ ክፍያ ሊጠይቅ፤ የታችኛው ተፋሰስ አገራትም ይህን ቅን ሃሳብ ሊደግፉ ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገራት የኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማት ለወንዙና ገባሮቹ ዘላቂ ፍሰት ዋስትና ስለሚሰጥ በዕውቀት፣ በገንዘብና በፖሊሲ ረገድ ሊደግፉ ይገባል ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም በ'ፓን አፍሪካዊ' መንፈስ ሌሎች አገራትም እንዲጋሩት የማድረግ እንቅስቃሴ እንዳለም ተናግረዋል።

በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ላይ ከሚሰሩ በርካታ የምርምር ተቋማት መካከል አንዱ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር እሸቱ ወንድሙ፤ የዓባይ ተፋሰስን ማልማት ካለው ሁለንተናዊ ፋይዳ አንጻር የግብጽና ሱዳን የውሃ ፖለቲካ ትብብር ላይ መሰረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ዶክተር አደፍርስ ወርቁ እና ዶክተር ሞቱማም አገራቱ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እስከተሳሰሩ ድረስ ለወንዞች ውሃ ዘላቂ ፍስት ትብብር እንጂ ንትርክ እንደማያሻቸውም ገልጸዋል።

ግብጽ በመጪው ህዳር 2015 ዓ.ም ከ100 በላይ አገራት መሪዎች የሚሳተፉበትና የዘርፉ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች የሚታደሙበትን 27ኛውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ እንድታካሂድ ተመርጣለች።

ኢትዮጵያም በዚህ መድረክ እስካሁን ስላከናወነቻቸው የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች አስፈላጊውን መረጃ በመሰነድ በመድረኩ ላይ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተግባቦት ሥራ መሥራት እንደሚጠይቃት ገልጸዋል።

በመድረኩ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የምታካሂደው ልማት ሌሎችን ለመጉዳት አለመሆኑና ይልቁንም የተፋሰሱ አገራት የኢትዮጵያን የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት እንዲደግፉ ለመሞገት ከወዲሁ መዘጋጀት ይጠበቅባታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም